የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት አገርን አንጂ የመጡበትን ተቋምና ማንነት አይወክሉም – ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

1391

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 በአዋጅ በተቋቋመው የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት የኢትዮጵያን ህዝብ እንጂ የመጡበትን ተቋምና ማንነት እንደማይወክሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ኮሚሽኑ መንግስታዊ ጣልቃገብነት ሳይኖርበት በጥናት ላይ የተመሰረተና ትውልድ ተሻጋሪ ተግባር እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡ በአዋጅ በተቋቋመው የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ጋር የመጀመሪያ የትውውቅ መድረክና የስራ መመሪያ ምክክር ዛሬ ተካሂዷል።

የትውውቅ መድረኩን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ እንዳሉት ኮሚሽኑ መንግስት እያደረገ ባለው በፍትህ ስርዓት ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ፕሮግራሞች ለማሳካት፣ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሆን ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ የወሰን ማንነትና የራስ አስተዳድር ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለመ ነው።

የወሰን፣ ማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች ባለፉት ዓመታት እንደተመለሱ አድርጎ መቁጠር ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለግጭትና ቁርሾ ምክንያት የሆኑ ጥያቄዎችን ታሪካዊ፣ ህጋዊና ህዝባዊ በሆነ መንገድ ትውልድ ተሻጋሪ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ ነው የገለጹት። 

የኮሚሽኑ አበላት ስብጥርም ከወጣት እስከ አንጋፋ ያሉትን ጨምሮ ኃይማኖትን፣ ጾታንና የትውልድ አካባቢን እንደዚሁም ልምድና ዕውቀት ያላቸውን ግለሰቦች ያካተተ መሆኑን ገልጸው፤ አባላቱ ግን የመጡበትን ማንነትና ተቋም አይወክሉም ብለዋል።

አስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር

ስለሆነም ህሊናዊ፣ ገለልተኝነት፣ አሳታፊና በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ ከኮሚሽኑ እንደሚጠበቅ ነው ያብራሩት።

“ይህ አገር ፈርሶ ዳገም መሰራት አይችልም” ያሉት አቶ ደመቀ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምስጉን ለወጥ እያመጣን ባለበት ሰዓት ለውስጥ ገመናችን ስር ነቀል መፍትሄ በመስጠት ታሪካዊ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ከአባላቱ የተለያዩ አስተያይትና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሳታፊዎች ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል ህገ መንግስቱን የሚነኩ ጥያቄዎች እንዴት ይፈታሉ፤ ስለኮሚሽኑ አሰራርና የሶሰት ዓመታት ተግባር፣ አገር አቀፉ ህዝብና ቤት ቆጠራውና ምርጫው በኮሚሽኑ ስራዎች ጋር ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ ሰለኮሚሽኑ ገለልተኝነትና ነጻነት ጥቂቶቹ ናቸው።

ኮሚሽኑ የሚፈለገውን ተልዕኮ ለማሳካት የራሱን አደረጃጀት መፍጠር፣ ንዑሳን ኮሚቴ ማዋቀርና የስራ ክፍፍል ማድረግና መመሪያ ማዘጋጀት እንደሚችል ገልጸዋል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአሰራር ደንብ በአፋጣኝ አንደሚወጣለትም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የሶሰት ዓመታት የስራ ዘመን ቢኖረውም ሁሉም ተግባሩን አጠራቅሞ መጨረሻ ላይ ሪፖርት ማቅረብ ሳይሆን አስቸኳይ መፍትሄ የሚሰጣቸው አገራዊ አንገብጋቢ ጉዳዮች እቅድ ተይዞላቸው በየወቅቱ መፍትሄ እየተሰጣበችው እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

ህገ መንግስቱን የሚነኩ ጥያቄዎችን በተመለከተም “ከሰማይ በታች ሁሉም ነገር ኮሚሽኑ በጥናት ላይ ተመስርቶ ማንሳት ይችላል” ያሉት አቶ ደመቀ፤ ጥያቄዎቹ ግን ህገ መንግስቱን ማዕቀፍ መነሻ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ከተቋማት ግንኙነት አኳያም የኮሚሽኑ ሪፖርት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለአስፈጻሚው አካል እንደየሚመለከተው ጉዳይ ምክረ ሃሳብ ተወስዶ ይወሰናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆንም የሰላም ሚኒስትር አስፈላጊ ቴክኒካል ድጋፍ እንደሚያደርግለትም ተገልጿል።

“ከዚህ በፊት የመጣንበት መንገድ አዋጭ አይደለም፤ መንግስት በኮሚሽኑ ጣልቃገብነት እንደማይገባ አረጋግጠዋል” ሲሉም ቃል ገብተዋል።

በቀጣይ ወር ለሚደረገው ህዝብና ቤት ቆጠራም ታአማኒ ቆጠራ እንዲካሄድና ለኮሚሽኑ ስራ አስፈላጊው የሆነው ድጋፍ በፍጥነት እንደሚደረግ አቶ ደመቀ አብራርተዋል።

ከአስተያይት ሰጭዎቹ መካከል የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና   ፕሮፌሰር ፍስሃጽዮን መንግስቱ የኮሚሽኑ ነጻነት እንዲጠበቅ፣ አባላቱም የተቋማቸውንና ግላዊ ማንነታቸውን ሳይሆን ለትውልድ የሚተርፍ ጠቃሚ ተግባር እንዲያከናውኑ አስተያይታቸውን ሰጥተዋል።

ዶክተር ሙላት ተሾመ በበኩላቸው  የኮሚሽኑ አባላት ከተለያየ ባክግራውንድ የመጡ በመሆናቸው ብዙ መስራት የሚቻል ይመስለኛል ብለዋል።  የመጣንበትን ተቋም ወይም ማንነት ወክለን ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ፤ ኢትዮጵያችንን ወክልን ነው የምንሰራው። ስለዚህ ከዚህ አካል የሚጠበቀው ከፍተኛ ስራ ነው ማለት ይቻላል ብለዋል።

ፕሮፌሰር ፍስሃጽዮንም ይሄ ትልቅ አደራ ነው፤ ትልቅ ሃላፊነት ነው።ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ቅንነትና የሃሳብ ነጻነቶች የሚያስፈልገው ስራ ነው በመሆኑም  ለሚመጣው ትውልድ በማሰብ የማንንም ፓርቲ አባላት ልንሆን ፣ ማንም ልንሆን እንችላለን ግን ተቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሆም ለሚመጣው ትውልድ አስበን ነው መስራት ነው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ብለዋል፡፡

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ከአባላት መካከል ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በቅርቡ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ ፤ ለኮሚሽኑም ጽህፈት ቤት ይቋቋምለታል ተብሏል።