ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኝው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መስጠትን አስመልክቶ በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ አቀረቡ

667

አዲሰ አበባ የካቲት 5/2011 ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኝው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መስጠትን አስመልክቶ በቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ዙር መቃወሚያቸውን አቀረቡ።

አቃቤ ሕግ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ላላስተማራቸውና ባልተቀረፀ ስርአተ ትምርት ሐሰተኛ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪዎች እንዲሰጥ አድርገዋል ባላቸው የቀድሞው የብረታብረትና ኢንጂኒየሪንግ (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱ የሚታወቅ ነው።

ሀሰተኛው የትምህርት ተቋም በአሜሪካ ከሚታወቀው የካሊፎርኒያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር ተቀራራቢ በሆነ ስያሜ የማስተርስና ዶክትሬት ዲግሪዎች ለማስተማር መኮንን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በተባለ ተጠርጣሪና ባልተያዘ ግለሰብ መቋቋሙን ክሱ ያስረዳል፡፡

ግለሰቡ ራሱን የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አድርጎ በማቅረብ፣ ከቀድሞ የሜቴክ ኃላፊዎች ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትለ፣ ሻለቃ ገብረ ሥላሴ ገብረ ጊዮርጊስ፣ ሻለቃ ፋሲል አበራ፣ መቶ አለቃ ቶማስ ደረሰ፣ ወሰን የለህ ኃይለ ሚካኤልና ሀድአት ወልደ ትንሳይ በተባሉ የተለያዩ ክፍል ኃላፊዎች ጋር በጥቅም ተመሳጥሯል።

በዚህም ሐሰተኛው ተቋም ከሜቴክ ጋር ከፍተኛ ትምህርት ለማስተማር የውል ስምምነት መፈራረሙንና ዋና ዳይሬክተሩ እንዲፀድቅ ማድረጋቸውን በክስ መዝገቡ ላይ ተብራርቷል። 

የሐሰት ኮሌጁ በታዳሽ ኃይል፣ በኦፕሬሽን ማኔጅመንትና በኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚክስ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪዎች ለመስጠት አራት ውሎችን ፈፅሟል።

በዚህም ተከሳሾቹ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ሐሰተኛ ተቋሙ አሜሪካ ውስጥ በከፈታቸው የሒሳብ ቁጥሮች ገቢ ማድረጋቸውንና በእጅ አዙር የጥቅሙ ተካፋይ በመሆናቸው፣ ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ዓቃቤ ሕግ መሥርቶባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ሜጀር ጄኔራል ክንፈ፤ ማርዳ መለስ ለተባለች ግለሰብ በሁለት ዙር 1,250,886 ብር ክፍያ ከሜቴክ እንዲከፈል በማድረጋቸው፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

በዚህ መዝገብ ተከሳሽ የሆኑት ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኝው ባቀረቡት መቃወሚያ የቀረበው የክስ ማመልከቻ የወንጀሉን የድርጊት ክፍል እና ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር ጉደለት ያለበት፣ ተጠቅሶ ከቀረበው የሕግ ድንጋጌ አነጋገር ጋር የማይጣጣምና ግልጽነት የጎደለው ነው ሲል   ያስረዳል።

ከሳሽ አቃቤ ሕግ ከገለፃቸው ድርጊቶች መካከል አስቀድሞ በመገናኘትና በመወሰን በመመሳጠር ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ በመከፋፈል ጥቅምን በእጀ አዙር የተካፈሉ በመሆናቸው የሚሉ ፍሬ ነገሮችን የገለፀ ቢሆንም መቼ፣ የት ቦታ፣  ምን ተብሎ እንደተወሰነ በእጅ አዙር ሚስጥራዊ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ክሱ አይገልጽም ሲል በመቃወሚያው ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል ተጠቃሽ ነው።

በተጨማሪም ከሳሽ አቃቤ ሕግ በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የማይታወቅ ሃሰተኛ ትምህርት ተቋሙን በመጠቀም የከፍተኛ ትምህርት የማስተማር ሽፋን የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ በማሸሽ ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ጥቅሙን ለመከፋፈል በማሰብ በሚል የቀረበው የክስ ዝርዝር ከሳሽ ጠቅሶ ካቀረበው ደንጋጌ ጋር ፈጽም የማይገናኝ መሆኑንም ያትታል።

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕግን ምላሽ ለመስማት ለየካቲት 11 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።