የኦነግ ሰራዊት አባላትን ወደካምፕ የማስገባቱ ተግባር ነገ ስምሪት ይጀመራል

93

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 የኦነግ ሰራዊት አባላትን ወደ ካምፕ የማስገባቱ ስራ  ነገ ስምሪት እንደሚጀመር ተገለጸ።

በኦነግና መንግስት መካከል ለወረደው እርቀ ሰላም የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ሁለቱ አካላትና አባ ገዳዎች በተገኙበት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሰላማዊ የፖለቲካ ሁኔታና በመንግስት በተደረገው ጥሪ መሰረት ወደ አገር ቤት ከገቡት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ይገኝበታል።

ሆኖም የኦነግ ሰራዊትን ወደ ካምፕ ከማስገባት ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ተፈጥረው በተለይም በምእራብና ደቡብ ኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር ተፈጥሮ ቆይቷል። 

ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታትም በአባ ገዳዎች ሸምጋይነት በመንግስት እና በኦነግ መሪዎች መካከል እርቅ ወርዶ የቴክኒክ ኮሚቴም ተቋቁሟል።

ኮሚቴው ከአባ ገዳዎች ጋር በመተባበር እርቀ ሰላም እንዲወርድ ጥረት የተደረገ ሲሆን  ኦነግም ሰራዊቱን ወደ ካምፕ ለማስገባት መስማማቱ ይታወሳል። 

የቴክኒክ ኮሚቴው እና የሁለቱ ወገን ተወካዮች ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የኦነግ ሰራዊት አባላትን ወደ ካምፕ ለማስገባት የሚሄደው ቡድን ከነገ ጀምሮ ወደ 12 ዞኖችና 22 የተመረጡ ወረዳዎች እንቅስቃሴ ይጀመራል። 

በዚሁ ወቅት የኦነግ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ እንደተናገሩት የሰራዊቱ አባላት ወደካምፕ እንዲገቡ ድርጅታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)ን ወክለው የተገኙት አቶ ሞገስ ኢደኤ በተመሳሳይ መንግስት የቴክኒክ ኮሚቴውና አባገዳዎቹ ዘላቂ አርቀ ሰላም ይወርድ ዘንድ የሚያደርጉት ጥረት እንዲሳካ ተገቢውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት ለኦሮሚያ ክልልም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል ከኦነግ ባሻገር ካሉ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋርም በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሞገስ፤ መላው ህዝብም የተጀመረው እርቀ ሰላም ከግብ ይደረስ ዘንድ በሙሉ ልቡ ድጋፉን አንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የአባ ገዳዎቹና ቴክኒክ ኮሚቴ ተወካይ አቶ ኃይሌ ገብሬ በበኩላቸው የአባገዳዎቹና የቴክኒከ ኮሚቴው ተልእኮ እንዲሳካ ሁለቱም ወገኖች ላሳዩት ተባባሪነትና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም