መቀሌ ሰባ እንደርታ ድሬዳዋ ከነማን 2 ለ 1 አሸነፈ

279

ድሬዳዋ የካቲት 5/2011 በ16ተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው በመቀሌ ሰባ እንደርታ 2ለ1 ተሸነፈ።

የመቀሌው ሰባ እንደርታ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በሁለተኛ አጋማሽ የተሻለ በመጫወታችን አሸንፈናል” ሲሉ የድሬዳዋ አሰልጣኝ “ሙሉ በሙሉ ተበልጠን ተሸንፈናል” ብለዋል፡፡

በብዙ ሺህ ደጋፊዎች ታጅቦ የተካሄደው የመቀሌ ሰባ እንደርታና የድሬዳዋ ከነማ ጨዋታ ማራኪ ካለመሆኑ በተጨማሪ ፍትጊያና መጎሻሸም የበዛበት ነበር፡፡

አልፎ አልፎ ወደ ግብ ከመጠጋት በስተቀር ጥሩ ሙከራዎች ያልታየበት ቢሆንም በ20 ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከነማ ራም ኬሎ ያገኛትን ኳስ ጎል አስቆጥሮ 1 ለ 0 በመምራት ለእፍረት ወጡ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ መቀሌ ከነማ ወደ ግብ በመጠጋት የተሻለ ሲሆን በ54ተኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ጎል አስቆጥሮ መቀሌን አቻ አድርጓል፡፡

በ91ኛው የባከነ ደቂቃ ላይ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ሁለተኛውን ጎል በማስገባት መቀሌን አሸናፊ ማድረግ ችሏል፡፡

ከጨዋታ በኋላ የመቀሌው ዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ “ከእረፍት በኋላ በቡድኑ ውስጥ የነበረውን መረበሽ አስወግደን በመጫወታችን አሸንፈናል” ብለዋል፡፡

“ጥሩ ፉክክርና  አሳይተናል፤ አሸንፈን የፕሪሚየር ሊግ መሪ በመሆናችን ተደስቻለሁ” ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ከነማ ዋና አሰልጣኝ ስምኦን አባይ ቡድናቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ከጨዋታ በታች መጫወቱና ትኩረት በማጣቱ መሸነፋቸውን ተናግረዋል፡፡

” የመቀሌ ቡድን ተጨዋቾች ተደራጅተው ያጠቃሉ፤ ሙሉ በሙሉ ተበልጠን ተሸንፈናል” ብለዋል፡፡

በቀጣይ ያለባቸውን ክፍተት አርመው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የቀሯቸዋል ፡፡