ጉባኤው ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል – የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

386

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 በአዲስ አበባ የተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም መጠናቀቁን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። 

ኮሚሽኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የፌደራል ፖሊስ ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ፣ የደህነት መዋቅሩ በቅንጅት መስራታቸው ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ የጎላ ሚና ተጫውቷል።

በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ላይ 35 ፕሬዝዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች በርካታ ቁጥር ያላቸው የልዑካን ቡድን አባላት ተሳትፈዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ መላኩ ፋንታ መግለጫውን ሲሰጡ እንዳሉት ፤ ስብሰባው ያለምንም የጸጥታ ችግር ተጠናቋል።

ለዚህም ደግሞ ጉባኤው ከመካሄዱ በፊት ኮሚሽኑ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

አንዲያውም ከበፊቱ በተለየ መንገድ ከመዝጋት ይልቅ ክፍት እንዲሆን መደረጉን የገለጹት ኃላፊው የመንገድ ዳር የደህንነት ካሜራዎች ተተክለው በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።  

የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም የደህንነት መዋቅሩ በቅንጅት መስራታቸው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጎላ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

በተለይ ኀብረተሰቡ ለጉባኤው ታሳታፊዎች ቅድሚያ በመስጠትና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር ላሳየው ቀና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል። 

እንደ ኃላፊው ገለጻ በቀጣይም የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረው የመከላከያ ቀን በስኬት እንዲካሄድ ፌደራል ፖሊስ ከመከላከያ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።