ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠር ይገባል....ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

111

ሀዋሳ የካቲት 5/2011 የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት የሚገኘውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠር እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በደቡብ ክልል ለአንድ ዓመት የሚቆይ የታክስ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

ንቅናቄው በይፋ ሲጀመር የገቢዎች ሚንስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ከብድርና እርዳታ ተላቆ የራስን የልማት ወጪ በራስ የገቢ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ሀገራዊ ጥረት በሁሉም ደረጃ ሊጠናከር ይገባል።

ሀገሪቱን እየተፈታተነ ያለውን የግብር ስወራ፣ ማጭበርበርና የኮንትሮባንድ ንግድ በመከላከል የነገይቱን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ በተሰማራበት የሥራ መስክ ከሚያገኘው ገቢ ግብሩን በመክፈል ተገቢውን ግዴታ መወጣት እንዳለበትን አስገንዝበዋል።

ሀገርና ህዝብን መውደድ በተግባር ሊተገበር እንደሚገባና ለእዚህም ከታክስ ስወራ፣ ማጭበርበርና ህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ራስን በመጠበቅ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ አጋርነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ በበኩላቸው የክልሉ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት መሰብሰብ ያለበትን ያህል ባይሆንም ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በ2006 ዓ.ም በክልሉ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ይሰበሰብ ከነበረበት በ2010 ዓ.ም 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በተደረገ ጥናትም በዓመት እስከ 15 ቢሊዮን ብር በክልሉ መሰብሰብ እንደሚቻል ከተደረሰበት ውጤት አንጻር ግን ገና ብዙ እንደሚቀር ገልጸዋል።

ከኢኮኖሚው አንጻር ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ያልተቻለባቸው ምክንያቶችንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

እንደእርሳቸው ገለጻ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መበራከት፣ የግብር ከፋዩ ለህግ ተገዥነት ደረጃ እጅግ አነስተኛ መሆን፣ የግብር ሰብሳቢው የማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ የመረጃ አደረጃጀት አስተዳደርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጉድለት በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበትም አቶ ንጉሴ አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ በበኩላቸው እንዳሉት  የክልሉ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ልክ ገቢ መሰብሰብ ባለመቻሉ እያደገ የመጣውን የክልሉ መንግስት የወጪ ፍላጎት በአግባቡ ማሟላት አልተቻለም።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በርካታ የማህበራዊ አገልግሎት፣ የአዳዲስ ኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ግቦች ላይ  በሚፈለገው ደረጃ መድረስ አለመቻሉንም አመልክተዋል።

በመሆኑም የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግና የታክስ ስርዓቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት በቂ ገቢ በመሰብሰብ ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በዘርፉ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መመከት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"ልማታዊ የታክስ ስርዓት በመገንባት የታክስ ፖሊሲ አላማዎችና መርሆዎችን ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ ነው" ሲሉም ገልጸዋል። 

ዛሬ በይፋ በተከፈተውና ለአንድ ዓመት በሚቆየው ክልላዊ የታክስ ንቅናቄ መድረክ ላይ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት፣ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና የሙያ ማህበራት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የታክስ አምባሳደሮችም ተሰይመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም