የግብርና ምርት እሴት ተጨምሮበት ለገበያ ካልቀረበ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንደማይሆን ተገለጸ

75

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 የግብርና ምርት እሴት ተጨምሮበት ለገበያ ካልቀረበ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንደማይሆን በአፍሪካ ህብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽን አመለከተ።

ኮሚሽነሩ አምባሳደር ጆሴፋ ሊኦኔል ኮሬያ ሳኮ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአህጉሩ የሚመረተው ምርት እሴት ተጨምሮበት ለገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ ኢንዱስትሪውን ማስፋፋት ያስፈልጋል።

የአገር ውስጥ የገበያ ትስስርን በማጠናከር ወደ ቀጣናዊ የገበያ ትስስር መሸጋገር አስፈላጊ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጥገኝነት ለመላቀቅ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።

ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት የአፍሪካ ህብረት የተቀናጀ አሰራር እየተከተለ መሆኑንና የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽኑ ከኃይልና መሰረተ-ልማት ኮሚሽን ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ውሃ፣ ኤሌክትሪክና መንገድ እንዲስፋፋ እየተሰራ መሆኑንም ጭምረው ተናግረዋል ።

የአህጉሩን የግብርና ስራ ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አምባሳደር ጆሴፋ ሊኦኔል ኮሬያ ሳኮ ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ከዚህ ቀደም ለእርሻ ምቹ የነበረውን ዝናብ እያዛባው በመሆኑ አማራጭ መፈለግ የግድ በመሆኑ የመስኖ ግብርናን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት ከፖሊሲ ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ግብርናውን ለማዘመን እንቅፋት የሆነውን የገንዘብ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የግል ዘርፍ ተሳትፎን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

''ወጣቶችና ሴቶችን በግብርና ስራ ለማሳተፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል'' ነው ያሉት።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጋር ለአፍሪካ 'የዘላቂ ግብርና ማዕቀፍ' ባለፈው ጥቅምት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የማዕቀፉ ትኩረት የህብረቱ አባል አገሮች በአገር ደረጃ ሰፋፊ የእርሻ ስራ መስራት የሚያስችላቸውን ስትራተጂ ለመንደፍ የሚያስችል ነው።

ግብርናን ለማዘመን በወጣው የማላቡ ስምምነት መሰረት የአፍሪካ አገሮች ግብርናን ለማዘመንና ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰሩ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም