በማረሚያ ቤት "ለረዥም ጊዜ በፍርድ ለቆዩ ታራሚዎች ይቅርታ ይደረጋል" -የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

200
አዲስ አበባ ግንቦት 20/2010 የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በእስር ቆይታቸው "ረዥም ጊዜ ያሳለፉ ፍርደኞች የይቅርታ ህጉን ተከትሎ ይቅርታ" ተደርጎላቸው ከማረሚያ ቤቱ እንደሚወጡ ገለጸ። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር አባላት በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለመመልከት በዛሬው እለት ጎብኝተዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የይቅርታ መስፈርቱን የሚያሟሉና በማረሚያ ቤቶች ረዥም ጊዜ የቆዩ፣ የመታረምና የመጸጸት ባህሪ ያሳዩ ታሪሚዎችን በይቅርታ እንዲፈቱ ያደርጋል። የይቅርታ መስፈርቱ በእስር ጊዜያቸው የመታረምና መጸጸት ባህሪያ ያሳዩ፣ በማይድን በሽታ የተያዙ፣ እድሜያቸው የገፉ፣ ተደጋጋሚ ወንጀል ያልፈጸሙ፣ ከሶስተኛ ወገን ጋር እርቅ የፈጸሙ ወይም እርቅ ለመፈጸም የሞከሩ እንዲፈቱ ይፈቅዳል። በተለይ በሰሩት ወንጀል ምክንያት ተፈርዶባቸው ህጻናት ልጆች ይዘው የታሰሩ ሴቶች "ጉዳያቸው ታይቶ በልዩ ሁኔታ የሚፈቱበት ሂደት ይኖራል" ብለዋል። በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ በአሁኑ ወቅት "ይቅርታ እየተሰጠ ያለው ትላልቅ ወንጀል ለፈጸሙ ብቻ  ነው" የሚል የተሳሳተ ሃሳብ መኖሩን ያወሱት ዋና ዐቃቤ ሕጉ፤ የፌዴራልና የክልሎች መንግስታትም ከአሁን በፊት  በተለያዩ ወቅቶች ለበርካታ ሰዎች "ይቅርታ" ሲሰጡ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። በአስገድዶ መድፈር ተከሰው ፍርደኛ የሆኑ ታራሚዎች ግን የይቅርታ አሰጣጡ ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ተናግረዋል። የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት የጥበቃ ደህንነት አስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ ዋና ኦፊሰር አለምነህ ተረፈ በበኩላቸው፤ በማረሚያ ቤቱ ከጊዜ ቀጠሮ እስከ ከባድ ፍርድ ተፈርዶባቸው የሚገኙ ታራሚዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል። እነዚህ ታራሚዎች በፍርድ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ጀምሮ "በተለያዩ አገራዊ ልማት ላይ የራሳቸውን አስተዋጾኦ እያደረጉ ይገኛሉም" ብለዋል። ከታራሚዎቹ መካከል መስፈርቱን የሚያሟሉት በፍጥነት ይቅርታ እንዲሰጣቸው ለማድረግ የተቀላጠፈ የመረጃ አያያዝና አደረጃጃት እንዲኖር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረል። በማረሚያ ቤቱ የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የመኝታና  የምግብ አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ በወቅቱ ተጠቁሟል። በቀጣይም በይቅርታ አሰጣጥና በፍትህ ተቋማት አገልግሎት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከታራሚዎች ጋር "በየጊዜው ውይይት ይደረጋል" ተብሏል። የአሁኑ የማረሚያ ቤት ጉብኝት በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር አባላት ደረጃ የመጀመሪያ ጉብኝት መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም