ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሴቶች በሳይንስ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ተባለ

1016

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የልማት ውጥኖችን በዘላቂነት ከግብ ለማድረስ ኢንጂነሪንግና ሂሳብን ጨምሮ የሴቶችን የሳይንስ ትምህርት ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ።

ሴቶች ከዓለም ህዝብ ቁጥር 50 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ቢይዙም በሳይንስና በምርምር ዘርፍ ያላቸው ተሳተፎ ግን ከ30 በመቶ በታች ነው።

በተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መረጃ መሰረት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2014 – 2016 በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ትምህርት መስኮችን የሚመርጡት ከ30 በመቶ አይበልጥም።

በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ 3 በመቶ፤ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በሂሳብና ስታቲስቲክስ 5 በመቶ፤ እንዲሁም በኢንጂነሪንግ፣ ማኑፋክቸሪንግና ግንባታ ደግሞ 8 በመቶ ብቻ እንደሆኑ መረጃው ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአስትሮኖሚና አስትሮፊዚክስ ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ ዶክተር ሚርጃና ፖቪች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሴቶች በሳይንስና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ ውስን ነው።

ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በሳይንስ ፣ ቴክኖሎጂ ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ የትምህርት ዘርፎች ሴቶች ቁጥር ከፍ ማለት እንዳለበት ገልጸዋል።

በዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ስር ካሉ 13 ሺህ 565 የአስትሮኖሚ ተመራማሪዎች መካከል ሴቶቹ 2 ሺህ 447 ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያና ስፔን ከአለም የተሻለ ብዛት ያላቸው ሴት የአስትሮኖሚ ተመራማሪዎች ቢኖሯቸውም፤ ከጠቅላላው የሴቶች ቁጥር አንፃር ሲታይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።

የአፍሪካ አገራትም ሴቶችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ምርምር ዘርፍ የማሳተፍ ልምዳቸው አናሳ መሆኑን ዶክተር ሚርጃና አስረድተዋል።

ቱኒዚያ 45 በመቶ ሴቶችን በማሳተፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን፤ ቻድ 5 በመቶውን ይዛ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች  ያሉት ተመራማሪዋ ፤ ኢትዮጵያ በመስኩ የሴቶች ተሳትፎ 14 በመቶ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አገራት የታቀዱ የልማት ግቦቻቸውን እውን ለማድረግ አካታች ፖሊሲዎችን መደገፍና አርአያ ሴት ምሁራንን በማብቃት የሴቶችን ሚና ማሳደግ ይገባለ ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ላቦራቶሪ ሳይንስ ትምህርት ክፍል አስተማሪና ተመራማሪ ዶክተር አስቴር ጸጋዬ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የስራ ጫና መብዛት፣ ከወንዶች በታች እንደሆኑ አድረጎ የመሳል የዳበረ ልምድ ወደ ኋላ ጉትቷቸዋል ይላሉ።

በኢትዮጵያ የሴቶች ተሳትፎ በሚኒስትር ደረጃ 50 በመቶ መድረሱን ያመለከቱት ዶክተር አስቴር በቁጥር አናሳ ቢሆኑም እስከ ፕሮፌሰር ማዕረግ የደረሱ ሴቶች መኖራቸውንና መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱ በአሁኑ ወቅት ያሉ መልካም አጋጣሚዎች ናቸው ብለዋል። 

በመሆኑም ሴቶች የእድገት መሰረቶች መሆናቸውን በመገንዘብ ወደ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ የትምህርት ዘርፎች ደፍረው እንዲገቡ ማበረታታት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ ሴቶችን እንደማይችሉ የሚቆጥረው ጎታች አስተሳሰብ እንዲወገድ፤ በራሳቸው የሚተማመኑና ‘እችላለሁ’ የሚል ወኔን ያነገቡ እንዲሆኑ ወንዶችም  አጋርነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ተብሏል።