በዘላቂነት ለመቋቋም አፋጣኝ የመንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች ገለጹ

50

የካቲት 5/2011 ከጊዜያዊ መጠለያ ወጥተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የመንግስት አፈጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በቤንሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖች ገለጹ።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዜያዊ መጠለያ ሰፍረው የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ የወለጋ ዩኒቨርሲቲና የነቀምቴ ከተማ ማህበረሰቦች ተናግረዋል። 

ወጣት በላይነህ  ገረመው በዞኑ ሳሲጋ ወረዳ ሀንገር መጠለያ ከሰፈሩት መካከል አንዱ ሲሆን ተፈናቅለው ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት ፣ የነቀምቴና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉላቸው የዕለት ደራሽ እርዳታና የመጠለያ ድጋፍ ህይወታቸው መታደግ  እንደቻሉ ለኢዜአ ገልጿል።

በተፈናቀሉበት ወቅት ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደሙጠና በሂደቱም ብዙ ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቶ “ በዘላቂነት የምንፈልገው መንግስት ይሆናችኋል ብሎ በሚወስደን አካባቢ የመኖሪያና የመስሪያ ቦታ ሰጥቶን መኖር ነው " ብሏል

ተፈናቅለው ሲመጡ የአካባቢው ህዝብ በተለይም ቄሮዎች ምግብና ሌላም የእለት ደራሽ እርዳታ በመስጠት ከፍተኛ እገዛ  እንዳደረጉላቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ ኡመር ሀሰን የተባሉት ተፈናቃይ ናቸው፡፡

አቶ መሰረት ደማሹ በበኩላቸው በጊዜያዊ መጠለያው  ሲደረግላቸው የቆየው የምግብ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡

ወይዘሮ ቢሽራ አህመድ የተባሉት ተፈናቃይ በበኩላቸው “ መጠለያው ለመኖር አመቺ  ባለመሆኑ  በብርድና ፀሐይ ስቃይ እየደረሰብን ነው፤ የሚቀርብልን እርዳታም በቂ አይደለም፤ መንግስት በሰላም እየኖርን ልጆቻችን ማሳደግ የምንችልበት አካባቢ እንዲያሰፍረን እንፈልጋለን” ብለዋል

ተፈናቃዮቹ እንደገለጹት አሁን ካሉበት ጊዜያዊ መጠለያ ወጥተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የመንግስትን አፋጣኝ ድጋፍ ይሻሉ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ብርሀኑ ኦልጅራ በሁለቱ ክልሉች አዋሳኝ አካባቢ ከ157 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በዞኑ 34 መጠለያ ጣቢዎች መስፈራቸውን ገልጸዋል።

ለተፈናቃዮች በመንግስት ስንዴ፣ ሩዝ፣ የምግብ ዘይትና የአልባሳት ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ገልጸው የአካበቢው ህብረተሰብም የበኩሉን  እገዛ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ብርሃኑ እንዳሉት ተፈናቃዮች ከብዛታቸው አንጻር ድጋፉ በቂ ባይሆንም አሁንም እርዳታው በየጊዜው እየተደረገላቸው ነው።

ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋምም ከማዕከል ከተላከው ቡድን ጋር ለተፋቃዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ቅደመ ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ገመዳ በበኩላቸው ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉት ወገኖች የአካባቢ ህብረተሰብ፣ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎችን እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዘላቂነት ለማቋቋምም  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማረጋጋት ሥራ ከመስራት ጎን ለጎን ሰርተው የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል

ቤት ንብረታቸውን ጥለው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ለመጡት ተፈናቃይ ዜጎች ተማሪዎች የስምንት ቀናት የሥጋ ፍጆታቸውን ትተው ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገረው ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ሕብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ናቶ በላቸው ነው።

የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ደሳለኝ በበኩላቸው ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከተፈናቃዮች ውስጥ 4ሺህ 200 የሚሆኑ ወገኖች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዲጠለሉ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ወላድ እናቶች፣ ነፍሰ ጡሮችና ህጻናት ነጻ የህክምና አገልገሎትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና 1ሺህ 200 ፍራሾችን እንዲያገኙ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ከመምህራንና ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር በመነጋገር ከወር ደወዛቸው 50 በመቶ ድጋፍ ማድረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ያሬድ፣ ዜጎች ተረጋግተው በቋሚነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ከመንግስት ጋር ለማመቻቸት ተቋሙ አስር አባላት ያሉት የጥናት ቡድን አቋቁሞ ወደዝግጅት ሥራ መግባቱን አስረድተዋል።

የነቀምቴ ነዋሪው አቶ ጌታቸው ለሜሳ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "  አቅም በፈቀደ መጠን ለልጄና ለቤተሰቤ የማደርገውን ለእነዚህ ወገኖችም ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤ መንግስትና እኛ ተጋግዘንህ ወደነበሩበት መመለስ አለብን" ብለዋል።

ተፈናቃዮችን ለመርዳት እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መንግስትና የተለያዩ አካላት ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ  የእዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ተሾመ ስብሀቱ ናቸው፡፡

ችግሮችን በመፍታት እነዚህን ዜጎች  በዘላቂነት ለማቋቋም  ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም