የጤና መድን ዋስትና አባል መሆናችን ፈጣን የሕክምና አገልግሎት እንድናገኝ አድርጎናል…ተጠቃሚዎች

1000

አክሱም የካቲት 5/2011 የጤና መድን ዋስትና አባል መሆናቸው ፈጣን የሕክምና አገልግሎት ከማግኘት ባለፈ ከአራጣ አበዳሪዎች ይደርስባቸው የነበረውን ብዝበዛ እንዳስቀረላቸው በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አንዳንድ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አሕፈሮም ወረዳ ጎርሁ ስርናይ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ወልዳይ ምስግና እንዳሉት፣ የጤና መድህን ዋስትና አባል በመሆናቸው ስምንት ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ህመም ሲገጥማቸው ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት እያገኙ ነው።

በዓመት አንድ ጊዜ በሚከፍሉት 240 ብር ብቻ የተለያየ አይነት የህክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን የተናገሩት አርሶ አደር ወልዳይ የጤና መድን አባል መሆናቸው ሲታመሙ ብድር ውስጥ ከመግባት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

በጤና መድን ዋስትና መታቀፋቸው ከድንገተኛ ወጪ፣ ካላስፈላጊ ብድርና ከአራጣ አበዳሪዎች ብዝበዛ እንዳላቀቃቸው የገለጹት ደግሞ በወረዳው ሆያመደብ ገጠር ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ገብሩ ግርማይ ናቸው።

ከእዚህ በተጨማሪ የጤና መድን አገልግሎቱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ነው አርሶ አደሩ ያመለከቱት።

በየዓመቱ በሚከፈለው አነስተኛ መዋጮ ከሰባት ቤተሰቦቻቸው ጋር ሙሉ የህክምና ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በመቻላቸው ደስተኛ ናቸው።

በአትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ የመቀሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብሩ በላይ በበኩላቸው የጤና መድን ዋስትና አባላት እርስ በራሳቸው ተጋግዘው የተሟላ የህክምና አገልግለት የሚያገኙበት አሰራር መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቅለ ተከላ፣ ማስዋብና የውጭ ሀገር የህክም አገልግሎት በስተቀር ሌሎቹ የህክምና አይነቶች የሚጠይቁትን ሙሉ ወጪ ለአባላቱ እንደሚሸፈን አመልክተዋል።

በተሽከርካሪና ሰው ሰራሽ ድንገተኛ አደጋዎች ጉዳት የሚደርስባቸው አባላት ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙም የጤና መድን ዋስትናው የህክምና አገልግሎቱን አስቀድሞ ማመቻቸቱን ተናግረዋል።

በጤና መድህን ዋስትና አባል ለመሆን በዓመት ለአንድ ጊዜ 240 ብር ብቻ እንዲከፍል የሚደረግ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል ለጤና መድን ዋስትና ህብረተሰቡ ያለው ዝቅተኛ ግንዛቤ ምክንያት በክልሉ ከሚገኙ 52 ወረዳዎች መካከል በጤና መድህን ዋስትና የታቀፉት ግማሽ ያህሉ ናቸው።