በዓሉ በጅግጅጋ ፣ ድሬደዋ ፣ወላይታ ሶዶ ከተሞች እና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

83
ጅግጅጋ/ድሬደዋ /ሶዶ/ አምቦ ግንቦት 20/2010 27ኛው የግንቦት 20 በዓል ዛሬ በጅግጅጋ ፣ ድሬደዋ  ፣ወላይታ ሶዶ ከተሞች እና  በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በፓናል ውይይቶች  ተከበረ፡፡ በዓሉ በጂግጂጋ ሲከበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐሙድ እንዳሉት ግንቦት 20 ለሶማሌ  ህዝብ የነፃነትና የእኩልነት ቀን ነው፡፡ የክልሉ ህዝብ ከግንቦት 20 ድል ወዲህ ሰላምና መረጋጋት፣ የውሃ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የሰው ኃይል ልማት ማሳደግ እና የባህል ግንባታ ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በርካታ የልማት ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም አሁንም ከህዝቡ የልማት ፍላጎት አንፃር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉ መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ አቅም በፈቀደ ሁሉ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዞን እና የወረዳ አመራሮችን ከትውልድ አከባቢያቸው ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች መንግሰታዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የተተገበረው አሰራር ጎሰኝነትን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን እና ሙስናን ለመታገል ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ "ዲብ ኦ ኦረሹ" ወይም እንደገና የመታደስ እንቅሰቃሴው  ከተተገበረ ወዲህ በደገህቡር፣ በሲቲና በፋፈን ዞኖች የነበሩ የጎሳ ግጭቶች መቅረቱንም ጠቁመዋል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉ መካከል ኡጋዝ መዓልን ፋራህ በሰጡት አስተያየት "በግንቦት 20 ድል አንባገነኑ ስርዓት ከተወገደ በኋላ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን እንቆማለን " ብለዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ሱልጣን አብዲከሪም ቀሌንሊ በበኩላቸው " ግንቦት 20 ለሶማሌ ህዝብ የነፃነት ቀናችን ነው፤ እኩል የዜግነት መብት ያገኘንበት ነው " ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በድሬደዋ ከተማ በዓሉ በፓናል ውይይት ሲከበር  በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት አመራሮች፣ የሠራዊት አባላትና የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ በበዓሉ ከተኙት መካከል ወይዘሮ ዘይነባ አህመድ በሰጡት አስተያየት "የግንቦት 20 ድል በቋንቋዬ እንድናገር፣ ባህሌን እንዳከብር ፤ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እኩል የልማት ተጠቃሚ እንድሆን ያስቻለ ታላቅ ቀን ነው" ብለዋል፡፡ የህዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች የሚበረታታና የግንቦት 20ን ውጤቶች ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው የገለፁት ደግሞ አቶ ሻሜ አቡበከር ናቸው፡፡ አቶ ጣሂር ሁሴን በበኩላቸው መንግስት  እየወሰዳቸው የሚገኙት ስር ነቀል የለውጥ መንገዶች የፌደራል ሥርዓቱንና የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት እየተወሰዱ የሚገኙ እርምጃዎች የዜጎችን እኩልነት፣ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ለዘላቂ ሰላምና  ለአንድነት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውና የግንቦት 20 ውጤቶችን የሚያጎላ መሆኑን የገለጸው  ወጣት አይናለም ማሞ ነው፡፡ የፓናሉን መድረክ የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራም ዑስማን ውይይቱ በፌደራዝም ሥርዓት አረዳድ ላይ የሚስተዋሉ የተዛቡ ግንዛቤዎችን በማስተካከል የተሻለ መግባባት ለመፍጠር ያገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወላይታ ዞን ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ሰራተኞችና የሶዶ ከተማ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በዓሉን በሶዶ ከተማ በፓናል ዉይይት አክብረዋል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉ መካከል  ወይዘሮ ታደለች ከለለ በሰጡት አስተያየት በተለይ የማህበረሰቡን የትምህርት ፍላጎት በመረዳት መንግስት በአከባቢው ዩኒቨርሲቲ በመክፈቱ ልጆቻቸው ሩቅ ቦታ ሳይሄዱ በአቅራቢያቸው በማስተማር ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት ጤራ በመድረኩ እንደተናገሩት ግንቦት 20 ህዝቦች በጋራ ባደረጉት ትግል ኋላቀርነትን አስወግደው የአመለካከት ልዩነቶች ህጋዊ መሰረት ባለው  መልኩ እንዲቻቻሉ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ህዝብ በትምህርት ፣ በጤናና በሌሎችም መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚነቱ ማደጉን ጠቅሰው " በእያንዳንዱ ዘርፍ ተግዳሮት እየሆኑ ያሉ የጥራት ጉድለቶችን እያረምን በዘላቂነት እንሰራለን " ብለዋል፡፡ የዞኑ ደኢህዴን ንዑስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘብዴዎስ ኤካ በበኩላቸው  ማህበረሰቡን የሚፈታተኑ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩልም የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ  በዓሉን በፓናል ውይይት ሲያከብሩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ መኩሪያ ገብረማሪያም እንዳሉት  ከመበታተን ተርፋ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀባትና  ዜጎቿ በአንድነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን መጠበቅ ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች የግንቦት 20 ድል ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው መሰረተ ልማቶችን በፈጣን  እድገት ከጫፍ እስከ ጫፍ በመዳረስ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት እንደ ሀገር  የነበሩት ሁለት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የለውጥ ኃይል የሆነው ወጣቱ ትውልድ የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ዴሞክራሲዊ አንድነት እንዲጎለብት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአደጋ ስጋት መከላከል የሶስተኛ ዓመት ተማሪ አብረሃም ወንድሙ በበኩሉ "አሁን የተገኘውን ሰላምና የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ እውን ለማድረግም  ሁላችንም ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል " ብሏል፡፡ ድሉን በዘላቂነት ለማስቀጠል   አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የእንግሊዘኛ መምህር  አቶ ጭምዴሳ ጉታ ናቸው፡፡ የስፖርት መምህርት አብዮት ደበላ በበኩላቸው የግንቦት 20 ድል ሴቶች በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት እድል የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ሰራተኛው  አቶ በቀለ ነጌሶ እንዳሉት የግንቦት 20 ድል በሁሉም  ዘርፍ እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በመድረኩ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሥርዓት ዋና ዋና ስኬቶችና ተግዳሮቶችን የሚገልጽ ጽሁፍ በምሁራን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም