አራት ተመራማሪዎች የክዋሜ ንኩሩማን የሳይንስ ሽልማትን አሸነፉ

1020

አዲስ አበባ ጥር 5/2011የአፍሪካ ኅብረት የ2018 የክዋሜ ንኩሩማ አህጉራዊና ክፍለ-አህጉራዊ ከፍተኛ ደረጃ የሳይንስ ሽልማትን ለአራት አፍሪካዊያን ተመራማሪዎች ሰጠ።

የሎሬት ሽልማቱ በህይወትና መሬት ሳይንስ እንዲሁም በመሠረታዊ ሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ የተከፈለ ነው።

በህይወትና መሬት ሳይንስ ዘርፍ አህጉራዊ የሎሬት ሽልማት አሸናፊ የደቡብ አፍሪካው ፕሮፌሰር ዴቪድ ማርክ ሪቻርድሰን ሲሆኑ በመሠረታዊ ሳይንስ ፣ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ አህጉራዊ የሎሬት ሽልማት ግብፃዊው ፕሮፌሰር አብደል-ሻፊ ፋህምያ ኦባዳ አሸንፈዋል።

እንዲሁም በህይወትና መሬት ሳይንስ ዘርፍ ክፍለ-አህጉራዊ የሎሬት አሸናፊዎች ደግሞ ቱኒዚያዊቷ ፕሮፌሰር ናዚሃ አቲ እና ደቡብ አፍሪካዊቷ ፕሮፌሰር አሌታ ሹቴ ናቸው።

ፕሮፌሰር ዴቪድ ማርክ ሪቻርድሰን የባዮሎጂና ሥነ-ምህዳር ተመራማሪ ሲሆኑ በ420 ጥናታዊ ጽሑፎች አዘጋጅና ተባባሪ አዘጋጅ ሆነው የተሳተፉና በርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን ያገኙ ናቸው። 

ፕሮፌሰር አብደል-ሻፊ ፋህምያ ኦባዳ የቁስ አካል መስተጋብር መስክ ተመራማሪ ሲሆኑ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1970ዎቹና 80ቹ የመጀመሪያው የጨረር ንድፈ-ሃሳብ አፍላቂ ከሆነው ሎሬንዞ ጋር በተባባሪነት ሰርተዋል።

ፕሮፌሰር ናዚሃ አቲ በበግና ፍየል እርባታና ጥራት ላይ ምርምር ያደረጉ ሲሆን በአምስት አገራዊና በስድስት ዓለም አቀፋዊ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፈዋል።

የፕሮፌሰር አሌታ ሹቴ የምርምር ትኩረት የደም ግፊት መጨመር በአፍሪካዊያን የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማድረግ ሲሆን በዘርፉ 250 ጥናት አድርገዋል።

የ2018 የክዋሜ ንኩሩማ አህጉራዊና ክፍለ-አህጉራዊ ከፍተኛ ደረጃ የሳይንስ ሽልማት ትኩረት ያደረገው የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ለማሳካት የተቀመጡ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራዎችን ለማሳካት ነው።     

አህጉራዊ የሎሬት ሽልማት አሸናፊዎቹ እያንዳንዳቸው 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላርና የምስክር ወረቀት ከወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር አብዱልፈታህ አልሲሲ ተቀብለዋል።

የክፍለ-አህጉራዊ የሎሬት አሸናፊዎቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው 20 ሺህ የአሜሪካ ዶላርና የምስክር ወረቀት ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ወስደዋል።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ግራዚያኖ ዳ ሲልቫ በአፍሪካ የግብርና ምርትን ለማሳደግ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር አብዱልፈታህ አልሲሲ የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።