አመልድ የገነባቸው የውሃ ተቋማት ተጠቃሚ እንዳደረጓቸው አርሶ አደሮች ገለጹ

65

ባህር ዳር  የኪታቲ  4/2011 የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) በአካባቢያቸው በገነባቸው ዘመናዊ የመስኖ ግድቦችና የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

ድርጅቱ በ2018 የፈረንጆች ዓመት ከ127 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የገነባቸው አነስተኛ የመስኖ ግድቦችና የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በዳንግላ ዙሪያ ወረዳ የብራቃት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዋሲሁን አምሳል ለኢዜአ እንደገለጹት ድርጅቱ የግዛኒን ወንዝ ለመስኖ አገልግሎት በማዋሉ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከሆኑ አራት ዓመታት ሆኗቸዋል።

በቀበሌያቸው የተገነባው የግዛኒ ዘመናዊ የመስኖ ግድብ ያላቸውን አንድ ሄክታር መሬት በገብስ፣ ሽንኩርት፣ ድንችና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

"በክረምት ዝናብን ጠብቄ ሳለማ በነበረበት ወቅት ለቤተሰቤ የሚበቃ ዓመታዊ ቀለብ እንኳ ለማግኘት እቸገር ነበር" ያሉት አርሶ አደር ዋሲሁን በአሁኑ ወቅት የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት ለመሙላት መቻላቸውን አስረድተዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ማክሰኝት ወረዳ የዘንጋጅ ማርያም ቀበሌ አርሶ አደር ስጦታው ፈንቴ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ከሆኑ አንድ ዓመት እንዳልሞላቸው ነው የገለጹት።

በፊት ንፅህናው ያልተጠበቀ ወራጅ ውሃ ከእንስሳት ጋር ለመጠቀም ይገደዱ ስለነበር ከነቤተሰባቸው ለተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታዎች ሲዳረጉ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

አርሶአደር ስጦታው እንዳሉት አመልድ የንፁህ መጠጥ ውሃ በአካባቢያቸው ገንብቶ ለአገልግሎት ካበቃ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የነበረባቸው የጤና ዕክል ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል።   

"የንፁህ መጠጥ ውሃ መጠቀም ከመጀመራችን በፊት ጃርድያን ጨምሮ በሌሎች ውሃ ወለድ አምጪ በሽታዎች እንጋለጥ ነበር" ያሉት ደግሞ የእዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ሙሏለም ባየ ናቸው።

አመልድ የዛሬ ሁለት ዓመት በቀበሌያቸው በገነባላቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ከሆኑ ጀምሮ ችግራቸው መቃለሉን ተናግረዋል።

በየጎጣቸው የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ዘላቄታዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻልም ተገቢ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑንም አርሶ አደሮች አስረድተዋል።   

የአመልድ የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ቀፀላ ንጉሴ በበኩላቸው እንዳሉት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከ127 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 270 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትና የመስኖ ግድቦች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ለአገልግሎት ከበቁት ውስጥ 12ቱ አነስተኛ ዘመናዊ የመስኖ ግድቦች ሲሆኑ እነዚህም  ከ227 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት አርሶ አደሮችን የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የዝናብ ዕጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች በቡድንና በግል አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 178 ኩሬዎችና በገመድ ፓምፕ የሚሰሩ የውሃ ጉድጓዶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት የተገነቡት የንፁህ መጠጥ ውሃና አነስተኛ ዘመናዊ የመስኖ ግድቦች 90 ሺህ የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚ አድርገዋል። 

አመልድ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው የልማት ስራዎች 5 ሺህ 491 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትና 236 አነስተኛ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረጉ ታውቋል።

ይህም ለክልሉ በዘመናዊ መስኖ የ16 ነጥብ 4 በመቶ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ ደግሞ የ11 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ማበርከቱንም ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ዋቢ አድርጎ የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም