ባንኩ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ድጋፍ አደርጋለሁ አለ

66

አዲስ አበባ  የካቲት 4/2011 የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የዜጎች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲናን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና የዜጎችን የአኗኗር ሁኔታን ማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲናን ባንኩ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውሰው፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ መስኖን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ነው የሚናገሩት።

ባንኩ በአገሪቷ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋትና ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል እንደሚያግዝም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በኢትዮጵያ በግብርናው መስክ የተሄደው ርቀት ብዙ ቢሆንም የተገኘው ውጤት ግን የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

ለዚህም ደግሞ አንዱ ማሳያ አሁንም የመቀጨጭ ችግር አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ መስኖን መጠቀም አማራጭ የሌለው መፍትኤ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም