የክፍለ አህጉራዊው የልማት ቢሮ መከፈት ፊፋ በእግር ኳስ ልማት እያከናወናቸው ላሉ ስራዎች አንዱ ማሳያ ነው – ጂያን ኢንፋንቲኖ

1014

አዲስ አበባ የካቲት 4/2011 የክፍለ አህጉራዊው የልማት ቢሮ መከፈት ፊፋ በእግር ኳስ ልማት እያከናወናቸው ላሉ ስራዎች አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ ገለጹ።

የእግር ኳሱ የበላይ አስተዳደሪ የሆነው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ የሚውለውን ክፍለ አህጉራዊ ልማት ቢሮ ዛሬ አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ አስመርቋል።

የልማት ቢሮው በውስጡ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የፕሮጀክት ማስተባባሪያ፣ የክፍለ አህጉራዊ ቢሮ ሃላፊ ጽህፈት ቤትና የቤተ መዛግብት ክፍሎች አሉት።

የልማት ቢሮው የቀጠናው እግር ኳስ አባል አገራት ከፊፋ ጋር በቅርበት በመስራት የእግር ኳስ ልማት ስትራቴጂዎችና ግቦቻቸውን እንዲያሳኩ ማድረግ ዋነኛው ስራው ነው።

ቢሮው ከአንድ ዓመት በፊት ተከፍቶ ስራ ይጀምራል ቢባልም ፊፋ ከመንግስት በኩል ያለውን ተነሳሽነት ለመመልከት እንደሚፈልግ በመግለጹና ለቢሮ የሚሆን ቦታ መፈለግ እንዲሁም የኪራይ ጉዳይ እንዲጓተት ማድረጉ የሚታወስ ነው። 

የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የእግር ኳስ አስተዳሪው አካል በማህበሩ አባል አገራት በኩል የእግር ኳስ ልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

እ.አ.አ በ2016 ፊፋ በጀመረው “የፊፋ ፎርዋርድ የልማት መርሃ ግብር” (The FIFA Forward Development Programme) እግር ኳስ በመላው ዓለም እንዲያድግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዛሬ በአዲስ አበባ የተከፈተው ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ የሚውለው ክፍለ አህጉራዊ ልማት ቢሮ የዚሁ ስራ አንዱ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሮው በአዲስ አበባ እንዲከፈት ላደረገው አስተዋጽኦና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአፍሪካ አገራት ላለፉት ሁለት ዓመታት የቀረጿቸው የእግር ልማት ፕሮጀክቶች ለአህጉሪቷ የእግር ኳስ እድገት ወሳኝ ሚና አንደሚኖራቸውና ፊፋም ለፕሮጀክቶቹ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ዛሬ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በሶስት ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችለውን የጋራ ስምምነትንም ፈርመዋል።

ስምምነቱ በአፍሪካ መልካም አስተዳዳርና በእግር ኳስ ውስጥ ያለውን ሙስና መዋጋት፣ በስታዲየሞች ጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እግር ኳስን ማስፋፋት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።

በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እግር ኳስን ማስፋፋት ለእግር ኳስ ልማቱ ወሳኝ ሚና እንዳለውና አፍሪካን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ 700 ሚሊዮን የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ፊፋ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዓለም እግር ኳስ እድገት የተሟላ እንዲሆን የአፍሪካን እግር ኳስ ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነና ለዚህም ፊፋ ከአፍሪካ ጋር በትብብር እንዲሰራ እንደሚያስችለውም ነው የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ ያስረዱት።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው የክፍለ አህጉራዊው ቢሮ መከፈት ፊፋ ከምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ አገራት ጋር በቅርበት ለመስራት ያስችለዋል ብለዋል።

የቢሮው መከፈት ፊፋ ከአባል አገራቱ ጋር የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማድረግና አገራቱ ከእግር ኳሱ አስተዳዳሪ አካል ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።

ፊፋ ከአባል አገራቱ ጋር ያለውን ቀረቤታ ይበለጥ ለማሳደግም ቢሮውን መክፈቱ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ፣ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራትና ለአፍሪካ አጠቃለይ እግር ኳስ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመላካች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በአገሪቷ እግር ኳስ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየትና ጥናት በማድረግ በጅምር ላይ ያሉ የእግር ኳስ ልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የፊፋ ምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ክፍለ አህጉራዊ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሚስ ማሪ ፍሎረንስ ማህዌራ ፊፋ የሰው ዘር መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ቢሮውን በመክፈቱ ትልቅ ደስታና ኩራት እንደሚሰማው ገልጸዋል።

ፊፋ ቢሮውን በኢትዮጵያ ከፍቶ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ እድገት ለመስራት መፈለጉ ለአፍሪካ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር እንደሆነም አመልክተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አባል አገራት በታዳጊ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች፣በሴቶች እግር ኳስ፣ፉትሳል፣የባህር ዳርቻ እግር ኳስና በአጠቃላይ ለአህጉሪቷ እግር ኳስ ልማት በትብብር መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

የስፖርት ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳም፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩዋ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አባል ሃገራት ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በልማት ቢሮው የምርቃት ስነ ስርአት ላይ ተገኝተዋል።

የክፍለ አህጉራዊው ቢሮው ካሉት የስራ ክፍሎች በተጨማሪ የእግር ኳስ ልማት ሃላፊ፣የፕሮጀክት አስተባባሪ፣የቴክኒክ፣የዳኞች እንዲሁም የፋይናንስና ስነ ምግባር ኦፊሰሮች ይኖሩታል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ስራውን የጀመረው የፊፋ ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮ ከዚህ ቀደም በሴኔጋልና በደቡብ አፍሪካ ከከፈተው ቢሮ ቀጥሎ ሶስተኛ ሲሆን የአዲስ አበባው ቢሮ ፊፋ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ክፍለ አህጉራዊ የልማት ቢሮዎች ቁጥር ወደ 10 ከፍ አድርጎታል።