ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲና ሲዳማ ቡና አቻ ተለያዩ

127

መቀሌ የካቲት 4/2011 ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲና ሲዳማ ቡና ዛሬ  መቀሌ ላይ ባደረጉት ጨዋታ ባዶ ለባዶ አቻ ተለያይተዋል።

ክለቦቹ ግጥሚያውን ያደረጉት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ግጥሚያ ነበር።

ክለቦቹ በትግራይ ስታዲዬም ያካሄዱት ጨዋታ ተመልካቾች የማይማርክና የረቡ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት እንደነበር የኢዜአ ሪፖርተር አመልክቷል።

የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አሰልጣኝ ፀጋይ ኪዳነማርያም በሰጡት አስተያየት ''በሜዳችን ማሸነፍ ነበረብን። ተጋጣሚያችን በመከላከል ላይ ያመዘነ ጨዋታ በመጫወቱ ያገኘነው ዕድል ባለመጠቀማችን ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል'' ብለዋል።

የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ''ነጥብ ተጋርተን መውጣታችን ጥሩ ነው። በቀጣይ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች የነበሩን ክፍተቶች አርመን ጥሩ ተፎካካሪ እንሆናለን'' ሲሉ ተናግረዋል።

በውጤቱ ሲዳማ ቡና  ነጥቡ  27 በማድረስ የሊጉን መሪነት ተቆናጧል።

የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ20 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስና መቀለ 70 እንደርታ በ26 ነጥብ በግብ ክፍያዎች ተበላልጠው ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ።

ስሁል ሽረ  15 ነጥቦች በማጠራቀም 15ኛ፣ደደቢት ደግሞ በ14 ነጥብ 16ኛ በመሆን የግርጌውን ሰንጠረዥ ይመራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም