''በሁሉም መስኮች የተጀመረውን ሀገር አቀፍ ለውጥ ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንሰራለን''- የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ

85

ድሬደዋ የካቲት 3/2011 በሁሉም መስኮች የተጀመረውን አገር አቀፍ ለውጥ ከዳር ለማድረስ እንደሚሰራ የምስራቅ ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

"ሕገ  መንግሥታዊ ታማኝነታችንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን!" በሚል መሪ የምሥራቅ ዕዝ ሠራዊት ቀን የማጠቃለያ በዓልን ዛሬ በድሬዳዋ ስታዲዬም በደማቅ ሥነ ሥርዓት አክብሯል፡፡

የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ  ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ በላይ በዚህ ወቅት እንዳሉት ሠራዊቱ በሁሉም መስኮች የተጀመረውን አገር አቀፍ ለውጥ ለማሳካት እንቅስቃሴውን ያጠናክራል።

ሠራዊቱ የአገርን ሉዓላዊነትና ክብር የመጠበቅ ታሪካዊና ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን እየፈፀመ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ሠራዊቱ በአዲስ አደረጃጀት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ግብዓት በመደራጀት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን እያጠናከረ ነው ብለዋል።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች  የሚፈጠሩ ችግሮችን በማርገብና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ሕዝባዊነቱን ባረጋገጠ መንገድ  ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ዋና አዛዡ ተናግረዋል።

የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ  ከሠራዊቱና ከጸጥታ አካላት ጋር እንዲቆም ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ጠይቀዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ሠራዊቱ የሀገር ደህንነት፣ ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ መንገድ ከመጠበቅ በተጨማሪ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በሚያከናወናቸው ተግባራት ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።

"በአገር አቀፍ ደረጃ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ፈጥኖ በመድረስ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ማድረጉ ሠራዊቱ የሕዝብ ደጀን መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ባለፈው ዓመት  በጅግጅጋና አካባቢው የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ በማረጋጋት ያከናወነው ተግባር የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ሁሌም እንደሚያስታውሱት ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦሪል በድሪ የአገሪቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሀዝቦች  መገለጫ የሆነው መከላከያ ሠራዊት በ''መደመር'' እሳቤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ግንባር ቀደም አሻራውን በማስቀመጥ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

"ለውጡ እንዲሳካ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ተቀናጅተንና እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለን" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለሠራዊቱ ተልዕኮ ስኬታማነት ክልሉ ድጋፍ እንደሚያሳደግ አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው በቅርቡ በድሬዳዋ የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ  በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የሠራዊቱ አባላትና መሪዎች ያከናወኗቸው ተግባራት የአገርና የሕዝብ ኩራት መሆናቸውን አረጋግጧል ብለዋል።

ለሰላምና ለሀገር እድገት ጠንቅ እየሆነ የሚገኘውን የኮትሮባንድ ንግድ  ለመከላከል ሠራዊቱና ሕዝቡ ተቀራርበው መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተዋል።

በበዓሉ ላይ የምሥራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች ፣ የአፋር ክልል ተወካዮች ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣የኃይማኖት አባቶች ፣ዑጋዞች ፣ አባገዳዎችና የድሬዳዋና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም