''በሁሉም ዘርፎች ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ማፍራት ወሳኝና ቀዳሚ ነው''-ሚኒስትር ሂሩት

65

ሐዋሳ የካቲት 3/2011 በሁሉም ዘርፎች ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ማፍራት ወሳኝና ቀዳሚ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ አስታወቀ።

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ትምህርት መስክ ለመጀመሪያ ጊዜ 104 ተማሪዎችን ትናንት አስመረቀ።

ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ  እንደተናገሩት ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን፤ አሸናፊ ሆኖ ለመዝለቅ ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ማፍራት ወሳኝና ቀዳሚ ነው።

ባለፉት ዓመታት የትምህርት ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ቢያድግም፤ ከጥራት አንጻር የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ በዕውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ሥነ ምግባር የታነጸ ብቁ ዜጎች ለማፍራት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

መዳን በሚቻል በሽታ ዜጎች እየሞቱ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ የሕክምና ምሩቃን ይህን ችግር ለማፍታት በሰለጠኑበት ሙያ በቅንነትና በታማኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ ዩኒቨርሲቲው በ53 የቅድመና ድህረ ምረቃ መርሐ ግብሮች 23 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ  ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲውን በምሥራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም  ተናግረዋል።

በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁና ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡ የህክምና ዶክተሮች በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማገዝ በሙያቸው ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያና የ10 ሺህ ብር ተሸላሚ የሆነው ዶክተር ዋቅሹም ፈጠነ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ለትምህርቱ ትኩረት ከመስጠቱ ባለፈ የመምህራንና የቤተሰቦቹ ድጋፍና ክትትል ለዚህ ውጤት እንዳበቃው ተናግሯል።

ሌላዋ የማዕረግ ተመራቂ ዶክተር ጋዲሴ አሰፋ በበኩሏ የህክምና ሙያ ትልቅ ትኩረት እንደሚጠይቅ ገልጻ፣በሙያው ሥነ ምግባር በቅንነት አገሯንና ወገኗን ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።

ኮሌጁ ካስመረቃቸው 104 ተመራቂዎች ውስጥ 34ቱ የህክምና ዶክተሮች በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር፣ 18ቱ በቀዶ ጥገና ነርሲንግ፣ 52ቱ በኅብረተሰብ ጤና ሶስቱ በድህረ ምረቃ የማህበረሰብ ጤና መስክ የተመረቁ ናቸው።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር ስራውን የጀመረው  በ2004 ነበር ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም