በአፋር ክልል የእናቶችና የህፃናት ሞት መቀነስን ጨምሮ አበረታች የጤና አገልግሎት ሽፋን ተፈጥሯል

73
አዲስ አበባ ግንቦት 20/2010 "ከዓመታት በፊት በጤና ተቋማት መውለድን ቀርቶ ሆስፒታል የሚለውን ቃል እንኳ አናውቅም ነበር፤ ዛሬ ተቋማቱን ከማወቅ አልፈን በአቅራቢያችን የአገልግሎቱን መጠቀም ከጀመርን ሰነባበትን፤" ይላሉ በአፋር ክልል በአርብቶ አደርነት ህይታቸውን የሚመሩት ወይዘሮ ሃዋ ጀላኒ። ወይዘሮ ሃዋ  ከሰመራ ከተማ በስተ ምስራቅ በምትገኘው አስቦዳ መንደር ከሰፈሩ በርካታ ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ሃዋ በመንደሩ መኖር ከጀመሩ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን በመንደሩ ያላቸው ህይወት ከበፊቱ በእጅጉ የተለየ ነው። እንደማንኛውም የአፋር ባህልና የአኗኗር ዘዬ ለዓመታት ከኖሩበት ተንቀሳቃሽ ቤት (ደሶ) ወጥተው በአሁኑ ወቅት ደረጃውን የጠበቀና የቆርቆሮ ክዳን ያለው መኖሪያ ቤት ቀልሰዋል። በአቅራቢያቸውም የጤና አገልግሎት ተቋማት በመስፋፋቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ቀደም ባሉት ዓመታት ከጤና ጋር በተያያዘ ይገጥማቸው የነበረው ችግር እየተቃለለ መምጣቱንም ነው የሚናገሩት። ነዋሪዎቹ የህይወታቸው መሰረት ከሆኑት እንስሳቶቻቸው ጋር ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የዘወትር ተግባራቸው በመሆኑ በሄዱበት ሁሉ የሚያጋጥማቸው የጤና ችግር በርካታ እንደነበርም ያስታውሳሉ። "ህፃናት በውሃ ጥም፣ በወባና በተላላፊ በሽታዎች ይጠቁብን ነበር፣ እናቶችም በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ ብዙ መከራ ይገጥማቸው ነበር፤" የሚሉት ወይዘሮ ሃዋ  ከተሳካ በባህል መድሃኒት ፈውስ ካልተሳካ ደግሞ ሞት ይጠብቃቸው እንደነበር ይናገራሉ። ወይዘሮ ሃዋ ጀላኒ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ሆስፒታል በቂ የጤና ክትትል አድርገው በቅርቡ ሴት ልጅ ተገላግለዋል። ሆስፒታሉ ለእናቶችና ህጻናት ጤንነትና የወደፊት መልካም ህይወት መሰረታዊ የሆኑ የህክምና ክትትል ማድረጉን ያደንቃሉ። "በአሁኑ ወቅት በመንደር ተሰባስበን ለከተማ ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ ስለሰፈርን ለሚያጋጥመን የጤና ችግር ባጭር ጊዜ ውስጥ ሆስፒታል መድረስ እንችላለን" ያሉት ወይዘሮ ሃዋ በተለይም በወሊድ ጊዜ የደም መፍሰስና መሰል ችግሮች ሲከሰቱ ያለ ምንም ስጋት የወላዷን ህይወት ማዳን መቻሉ ትልቅ ነገር መሆኑንም እንዲሁ። የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ አቶ ያሲን ሰዲቅ እንደሚሉት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የክልሉ የጤና ተቋማት ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር፤ እንዲያም ሆኖ እንኳ ህብረተሰቡ ያሉትንም ተቋማት በአግባቡ ለመጠቀም ፍላጎት አልነበረውም። በተለይ እናቶችና ህፃናት ዘንድ የከፋና እስከ ሞት የሚደርስ የጤና ችግር ያጋጥም እንደነበር የሚያስታውሱት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት በክልሉ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎትን በማስፋፋት ሁኔታውን ለመለወጥ በተደረገው ጥረት የእናቶችና ህጻናትን ጤና ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ለውጥ መምጣቱን ይናገራሉ። በክልሉ የጤና ሽፋንን ከማሳደግ አኳያ በርካታ ለውጦች መምጣታቸውንና የእናቶችና የህፃናት ሞትም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ይናገራሉ። አገሪቱ መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ካደረገች ጊዜ አንስቶ በተለይም በመሰረታዊ የጤና ተደራሽነት ላይ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችላለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም