102 የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማከናወኑን ማእከሉ አስታወቀ

109

የካቲት  3/2011- ለ102 ህሙማን የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማከናወኑን በጤና ሚኒስቴር ብሄራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማእከል አስታወቀ፡፡

ታካሚዎችና የኩላሊት ለጋሾች በበኩላቸው የኩላሊት ህክምና አገልግሎት ሊስፋፋና አሰራሩም ላይ ማሻሻያ ሊደረግለት አንደሚገባ ተናግረዋል፡፡  

የማእከሉ መስራችና ሜዲካል ዳይሬክተር  ዶክተር ሞሚና መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጨመር ለኩላሊት መድከም  መንስኤ እየሆነ በመምጣቱና ተገቢውን ህክምና አለመከታታል ጫና በማሳደሩ ከሶስት አመት በፊት ለማእከሉ መመስረት ምክንያት ሆኗል፡፡

ከብዙ ታዳጊ ሃገራት አኳያ ሲታይ በተጠቀሰው ጊዜ ለ102 ሰዎች ንቅለ ተከላ ማካሄድ “በጣም ከፍተኛ ስኬት ነው” ማለት ይቻላል ያሉት ዶክተር ሞሚና  ያለማቋረጥ በየወሩ ከ4-5 ሰዎች ንቅለ ተከላውን እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሆስፒታሉን ህክምና የመስጠት አቅም ለመገንባት ከላብራቶሪ፣ከራጅ ምርመራ፣ ከፓቶሎጂ አኳያ  ለንቅለ ተከላውን ታስበው የተሰሩ ስራዎች ባጠቃላይ የሆስፒታሉን አቅም ገንብተውታል ብለዋል፡፡

የንቅላ ተከላው ህክምና ቀጣይነቱም ታስቦበት እንደተገባ ገልፀው ከሰው ሃይል ግንባታ አኳያ ትኩረት ተሰጥቷል፤ ስራው ሲጀመር በአንድየኩላሊት ስፔሻሊስት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ስድስት መድረሳቸውንና በመማርም ላይ ያሉ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

“የኩላሊት ቀዶ ህክምና ባለሙያም አልነበረንም፣ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚቺጋን ጋር ሆነን እንሰራ ነበር”ያሉት ዶክተሯ አሁን ላይ አራት  የንቅለ ተከላ ሃኪሞች መኖራቸውንና ከነርሶችና ደጋፊ ባለሙያዎችም ዙሪያ አቅም የመገንባት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡

ማእከሉ የግብዓትና የቦታ ጥበት ችግር ቢፈታለት አሁን ከሚሰራው በተሻለ መልኩ አገልግሎቱን መስጠት ያስችለው ነበር ያሉት ዳይሬክተሯ እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረበ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

በማእከሉ ያገኘናት ወጣት ሳንያ ከድር ኩላሊቷን ለወንድሟ ለመለገስ መምጣቷን ገልፃ የተለያዩ ምርመራዎችን ማድረጓንም ተናግራለች፡፡

“ወንድሜ ዳይለሰሱን ከጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል” የምትለው ሳኒያ አፋጣኝ የንቅለ ተከላ ህክምናን ለማከናወን  መሰል ተቋማት እንዲበራከቱ መንግስትና ባለሀብቶች የተቀናጀ ስራ ሊሰሩ ይገባል ትላለች፡፡

የኩላሊት ታካሚዋ የ22 ዓመቷ ወጣት ሰብለወንጌል ሙሉጌታ በበኩሏ “ኩላሊት ከቤተሰብ ብቻ ነው የሚለገሰው” የሚለው ህግ  ኩላሊት እንዳታገኝ እንዳደረጋት ጠቁማ በቤተሰቧ ከእሷ የሚናበብ ኩላሊት ባለማግኘቷ መቸገሯን ጠቁማናለች፡፡

አቅም የሌላቸውና የሷን አይነት ችግር ሊገጥማቸው የሚችሉ ዜጎች አሁንም ያላቸው ምርጫ ሞት ብቻ በመሆኑ ህጉ ላይ የማስተካከል ስራ ሊሰራና በጎ ፈቃደኛ ከሆኑ ሰዎችና ሲሞቱ ኩላሊታቸውን ሊለግሱ ከሚችሉ ፍቃደኛ ሰዎች ኩላሊት የሚወሰድበት ሁኔታ በህጉ ሊካተት ይገባል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

ወይዘሪት ዘይነባ ሳሊያ ለእህቷ ኩላሊቷን ለመስጠት ምርመራዎችን እያደረገች እንደምትገኝ ገልፃ እህቷ ንቅለ ተከላው እስኪሰራላት ድረስ በሰዎች እገዛ ለኩላሊት እጥበት በሳምንት እስከ ስድስት ሺህ ብር እያወጡ መሆኑን ተናግራለች፡፡

አሁንም በርካታ ዜጎች ወረፋ በመጠበቅ ላይ እንዳሉ ማየቷን የምትናገረው ዘይነባ ይህ ጉዳይ በመንግስትም ሆነ በተለያዩ ድጋፍ ሰጪ አካላት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብላለች፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር  ዶክተር ሞሚና ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም በሀገራችን ከቤተሰብ ውጭ ኩላሊትን ለመለገስ የህግ ማእቀፉ እንደማይፈቅድ ተናግረዋል ፡፡

ሆኖም መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ  ማእከሉ  በሰው ሃይል እየጎለበተ ስለመጣ እንደ መፍትሄ ሁለት ቤተሰቦች ኩላሊት ለጋሽ ሆነው የደም አይነታቸው ባለመመሳሰሉ ምክንያት ንቅለ ተካላ ማካሄድ ሳይችሉ ሲቀሩ በተመሳሳይ ሰአት ኦፕሬሽኑን በማድረግ አቀያይሮ መስራት ላይ የህግ ማእቀፉ እንዲሻሻል እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ከሞተ ሰው ኩላሊት ለመውሰድ የህግ ማእቀፍ ማርቀቅ ያስፈለገዋል ያሉት ዶክተሯ በተለይ ህክምናችን ማደግና የሰው ሃይል መጨመር አለበት ለዚህም ከባርሴሎና በዚህ ዙሪያ የሰሩ ባለሙያዎችጋር ሄደቱን መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

ሰዎች ንቅለ ተከላ ሲደረግ የሚጠብቁት ወረፋ በሁለት መልኩ የሚታይ ነው ያሉት ዶክተር ሞሚና ለማያገግመው አይነት ኩላሊት የዳያሊስ አገልግሎቱን ማዳረስ ማሽኖችን በተወሰነ ሰዎች ብቻ ማስያዝ ስለሚሆን አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ሆኖም የተወሰነ የዳያላሲስ ህክምና ተደርጎለት ማገገም ለሚችለው ኩላሊት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ቅድሚያ ተሰጥቶ 24 ሰአት አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡

ጤነኛ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል፣አትክልትን በማዘውተርና በቂ ውሃ በመጠጣት የኩላሊት ህመምንም ሆነ ማንኛውንም በሽታ መከላከል እንደሚቻል ዶክተር ሞሚና ገልፀው በተለይ እድሜ ከገፋ በኋላ በየጊዜው የጤና ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትነም 102 የንቅለ ተካላ ህክምና ከተደረገላቸው ሰዎች 80 ከመቶ ያህሉ የኩላሊት ህመሙ መንስኤ ሳይታወቅ ኩላሊታቸው አንሶና ጠባሳ ፈጥሮ መገኘቱ በየጊዜው ህክምና ክትትል ያለማድረግ ክፍተት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ማእከሉ ከንቅለ ተከላ በመለስ ማንኛውም አይነት የኩላሊት ህመም  ህከምና እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

ማእከሉ ላቀረበው የግብአት አቅርቦት እጥረት ምላሽ የሰጡት የመድሃኒትፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ተሰፋአለም አድራሮ የማእከሉ የግዢ ፍላጎት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል ሲቀርብ እንደነበር አውስተዋል፡፡

ማእከሉ የግዢ ዝርዝር ያቀረበላቸው ባለፉት 2 ወራት መሆኑን ገልፀው ግብአቶቹ ከውጪ ሃገራት ተገዝተው የሚገቡ በመሆኑ በቅርብ ግዜ እንደማይደርሱ አመልክተዋል፤ሆኖም የህዝብ  አገልግሎት  እንዳይቋረጥ ኤጀንሲው የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶንዋይ ፀጋዩ ማእከሉ ያጋጠመውን የቦታ ጥበት አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ ሆስፒታሉ የጀመራቸውን  ሰፋፊ ግንባታዎች ማጠናቀቅ ላይ  ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው የማእከሉ ግንባታ በቀጣይ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም