የግሉ ዘርፍ የግዙፍ የልማት ድርጅቶች ተሳትፎን ለውጤት የሚያበቃ አሰራር መዘርጋት አለበት-- ምሁራን

60

ሀዋሳ የካቲት 2/2011 በግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የግሉን ዘርፍ የማሳተፍ ስራ በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ተገቢውን ቁጥጥር የሚያደርግ ተቋምና አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት አብላጫውን ድርሻ በመያዝ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል። 

በዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በልማታዊ ኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ አቶ ሃብታሙ ጌትነት እንደገለጹት ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶች መሰረታዊ ግብ የህዝብን ደህንነትና ልማትን ማረጋገጥ ነው።

“ተቋማቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈልጉ በመሆናቸው የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል”ብለዋል፡፡

የተቋማቱ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ይዞታ ስር መሆን ውጤታማ እንዳላደረጋቸውና እድገታቸውም ዘገምተኛ እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪው የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ሲደረግ ትርፋማነቱንና ወጪውን እየቀነሰ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የግሉን ዘርፍ የማሳተፉ ስራ በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ተገቢውን ቁጥጥር የሚያደርግ ህጋዊ ተቋምና አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ተቋማቱ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚከታተለው አካል ገለልተኛ መሆን አለበት ያሉት ተመራማሪው እንግሊዝና ቻይናን ለአብነት ጠቅሰው “በኢኮኖሚ የማደጋቸው አንዱ ሚስጢር ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ውስጥ የግሉን ዘርፍ ማሳተፋቸው ነው” ብለዋል፡፡

“መንግስት የወሰደው አቋም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ የሃገሪቱን የገንዘብ ችግር ከማቃለል ባለፈ ተቋማቱን በማዘመን ትርፋማ ሆነው የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋግጡ ያስችላል”ብለዋል፡፡

“ጠንካራ የግብይት ተቋማት መፍጠርና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ኢኮኖሚውን ለመለወጥ የተያዘውን እቅድ ያሳካል” ያሉት ደግሞ የምጣኔ ሃብት መምህሩ አቶ ስንታየሁ ሃይሉ ናቸው፡፡

ባደጉ ሃገራት የሚተገበርና አንዳንዶቹ ሲሰካላቸው በተከሉት የአሰራር ሂደት ውጤታማ ያልሆኑም እንዳሉ አንስተው “የኢትዮጵያ መንግስት አብላጫውን ድርሻ ይዞ ለመጀመር መሞከሩ ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡

የአተገባበር ሂደቱ ፖለቲካዊ ሃላፊነት የሚጠይቅና በህዝቡ ዘንድ ግልጸኝነትን በመፍጠር ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

“ሂደቱ በጥንቃቄ መመራት አለበት” ያሉት መምህሩ “ወደፊት በጠንካራ የግል ዘርፍ የሚመራ በኢኮኖሚ ያደገ ሃገር በመገንባት መንግስት የመከታተልና ሃገር የመምራት ድርሻውን ብቻ በተገቢው እንዲወጣ ያግዛል” ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጌታቸው አየለ በበኩላቸው እንደገለጹት ለውጭ ምንዛሪ ማነቆ የሆነውን የገንዘብ አቅም ለማጎልበት በግዙፍ ፕሮጀክቶች የግሉን ዘርፍ ማሳተፉ ጠቃሚ ነው፡፡

ደካማ በሆነ የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ ሽግግር ሲደረግ የሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ከዚህ ቀደም ተግባራዊ በተደረገባቸው የግል ባንኮችና ሌሎች ተቋማት መታየቱን አንስተው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ልሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ባህሪ ለይቶ ማጥናትና በተለይም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል”ብለዋል፡፡

“በሂደቱ የመንግስት ድርሻ ከፍተኛ ነው” ያሉት ዶክተር ጌታቸው በዘርፉ የሚሳተፉ የወጭ ባላሃብቶች በሚፈልጉት ልክ በቂ ባለሙያ ማፍራት እንዲቻል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

መንግስት በወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመንግስትና በግል አጋርነት እንዲገነቡ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም