የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ውጤት እየተገኘበት ነው----ግብርና ሚኒስቴር

118

ማይጨው የካቲት 2/2011 በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ አበረታች ውጤት እየተገኘበት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በትግራይ በክልል ደረጃ የሀሸንጌ ሐይቅን ከጥፋት ለመታደግ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ዘመቻ በኦፍላ ወረዳ መንከረ ቀበሌ ትላንት በይፋ ተጀምሯል።

በክልሉ ለ20 ቀናት የሚካሄደውን  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ያስጀመሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ናቸው፡፡

ዶክተር ካባ በወቅቱ እንደገለፁት በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመላ ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት ልማት አያያዝን ለማሳደግ የተያዘው እቅድ ውጤት እየተመዘገበበት ነው።

በመላ ሀገሪቱ የተፈጥሮ ደን ይዞታ በተጎዳበት 15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናውን የተያዘው ግብ እየተሳካ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል ።

" በክልሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተከናወነባቸው ስፍራዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው" ብለዋል ።

እንደ ዶክተር ካባ ገለጻ በተያዘው ዓመት በመላ ሀገሪቱ በሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለቀርቀሃ እፅዋት ልማት ትኩረት ተሰጥቷል።

ቀርቀሃ የአፈር መሸርሸርን በመጠበቅ በኩል ካለው ጠቀሜታ አንጻር ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የገለፁት ዶክተር ካባ  እያንዳንዱ ክልል ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆነ የቀርቀሃ ዝርያ መለየቱንም አመልክተዋል።

የኦፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ዝበሎ በበኩላቸው 1 ሺህ 465 ሄክታር ስፋት ያለው የአሸንጌ ሐይቅ ከሚያካልለው ተፋሰሳማ መሬት በ8 ሺህ ሄክታሩ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማካሄድ ታቅዶ ተገባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ 24 ከፍተኛና አነስተኛ ተፋሰሶች ላይ ለሃያ ቀናት በሚካሄደው የአፈርና ወሃ ጥበቃ ሥራም ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም