የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ከቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

66

አዲስ አበባ  ጥር 2/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቼን ዢያኦ ዴንግ ጋር ዛሬ ተወያዩ።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው እንደተናገሩት የሁለቱ ባለሰልጣናት ውይይት ያተኮረው  'ቤልት ኤንድ ሮድ' በተሰኘው የቻይና የውጭ ኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ላይ በሚመክረው ጉባኤ ላይ ነው።

ቤልት ኤንድ ሮድ የቻይናና አፍሪካ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና አጠቃላይ የኢኮኖሚ የትብብር ማዕቀፍ ለማጠናከር ተግባራዊ የተደረገ መርሃ ግብር ነው።

በመጪው ሚያዚያ ወር ቻይና በምታስተናደው በዚህ ጉባኤ ላይ  ኢትዮጵያ በሚኖራት የተሳተፎ ሚና ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተለየ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነቢያት የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ከተመሰረበት ጊዜ ጀምሮም ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ የቻይና ባለሀብቶች አፍሪካ ላይ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር በመሆኑ ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ተጠቃሚ እንደምትሆን አክለዋል።

ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቼን ዢያኦ ዴንግ የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም የክትትል ኮሚቴ ሊቀመንበርም ናቸው።

በተያያዘ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነሀ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞግረኒናን ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቷ የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ለሌሎች አገሮች መልካም ተሞክሮ መሆኑን ገልጸው በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የምጣኔ ሀብት፣ ፖለቲካና የፖሊስ ማሻሻያዎች ላይ  ህብረቱ ሙሉ ድጋፉን እንደሚያደርግ በዚሁ ወቅት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም