የግንቦት ሃያ ድል ራስን ከማስተዳደር ባለፈ የልማት ተጠቃሚ አድርጎናል… የድሬዳዋ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች

2776

ድሬዳዋ ግንቦት 20/2010 የግንቦት 20 ድል ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የተሻለ ዕድል መፍጠሩን የድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

አስተያየታቸው ለኢዜአ የሰጡት አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ከድሉ ውጤቶች ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን መንግስት ያለባቸውን የመንገድ ችግር እንዲፈታላቸውና ከእንስሳት ሃብታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡

በአስተዳደሩ ጀልዴይሳ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር ጀማል አህመድ እንደተናገሩት ባለፉት 15 ዓመታት  የጤናና የትምህርት ተቋማት በአካባቢያቸው በመገንባታቸው ብዙ ርቀት ሳይሄዱ መታከምና መማር ችለዋል፡፡

“በአሁኑ ወቅት የተበላሹ መንገዶች በአግባቡ እንዲሰሩልንና ከእንስሳት ሀብታችን በተሻለ ተጠቃሚ  መሆን እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡

“ባለፉት 27 ዓመታት በማንነታችን፣ በቋንቋችን፣ በባህላችን እንድንኮራና ልጆቻችን በቋንቋቸው እንዲማሩ ተደርጓል፤ የራሳችን ልጆችም ተምረው አካባቢያችንን እያስተዳደሩ ነው” ያሉት ደግሞ የብዬአዋሌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዩሱፍ አደም ናቸው፡፡

የኩላዩ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሸዲዴ ሃሚዶ በበኩላቸው ባለፉት ሃያ ዓመታት በኩታገጠም በሚገኙ ቀበሌዎች የማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች መስፋፋታቸውን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የግብርና ምርት እንዲጨምር የሚያስችሉ የምርጥ ዘር፣ የመስኖና የባለሙያ ክትትል በማግኘቱ ኑሮው እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡

” በአካባቢያችን ከሁለት ዓመት በፊት በተሰራ መስኖ በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ አትክልትና ፍራፍሬ እያመረትኩ ነው፤ አሁን ከተረጂነት ተላቅቄ የቤተሰቤን የምግብ ዋስትና አረጋግጫለሁ” ብለዋል።

የግንቦት 20 ድል በገጠር ለማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጸው ደግሞ የቃልቻ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት መሐመድ አህመድ ነው፡፡

“ባለፉት ሁለት ዓመታት ለወጣቱ የተመቻቸውን ብድር በመጠቀም ከጓደኞቼ ጋር በከብት ማደለብና በብሉኬት ሥራ ተሰማርተን ውጤት እያስመዘገብን ነው፤ ሌሎቹም የእኛን ፈለግ ለመከተል የገንዘብ ብድር አገልግሎት ስለጠየቁ መንግስት ድጋፉን ሊያጠናክር ይገባል” ብሏል።

የደበሌ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሚና አብዱራህማን በበኩላቸው የግንቦት 20 ድል ለሴቶች መብቶች መከበርና በየመስኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

“ቀደም ሲል የጤና ተቋማት በአካባቢያችን ባለመኖሩ ሴቶች በወሊድ ወቅት ለሞት ይዳረጉ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ጤና ተቋም በአቅራቢያ ስላገኘን ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሞት የለም፤ በእዚህም ጤናችን በተሻለ እየተጠበቀ ነው። ይሄ የግንቦት ሃያ ድል ውጤት ነው” ብለዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪ የግብርና ምርቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን የመኪና መንገድ ችግር እንቅፋት ሆኖበታል ያሉት ወይዘሮ አሚና፣ የሚስተዋለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርም እንዲፈታላቸው መንግስትን ጠይቀዋል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር በተለያዩ ገጠር ቀበሌዎች ተገኝቶ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት ባለፉት 27 ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና ያልተፈቱ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ በመንግስት በኩል ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የፖሊስና የፕላን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ተሰማ በበኩላቸው ነዋሪዎቹ ያነሷቸው ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸውን ገልጸው በሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ቀሪ ጊዜያት ለችግሮቹ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡