በአዳማ በህገወጥ መንገድ በመጋዘን የተከማቸ ከ1 ሺህ በላይ ጀሪካን ዘይት ተያዘ

123

አዳማ የካቲት 2/2011 በአዳማ ከተማ በህግወጥ መንገድ የተከማቸ ከ1 ሺህ በላይ ጀሪካን የምግብ ዘይት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክተር አስታወቀ።

በዳይሬክተሩ የምስራቅ ዲቪዥን ሻምበል ሶስት ምክትል አዛዥ ዋና ሳጂን ደብሩ ወልደተንሳይ እንዳሉት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3–28299 አ.አ በሆነ ኤፍ. ኤስ. አር ተሸከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ ባለ 20 ሊትር 220 ጀሪካን የምግብ ዘይት ትላንት በአዳማ አዲሱ መነሃሪያ አካባቢ ተይዟል።

ዘይቱን ሲያጓጉዙ የነበሩ አሽከርካሪና ረዳቱም በቁጥጥር ስር ውለው በተደረገባቸው ምርመራ ዘይቱን የጫኑበት መጋዘን መታወቁን ተናግረዋል።

ፖሊስ በደረሰበት መረጃ መሰረት ዛሬ  በአዳማ  ከተማ አንጋቱ ቀበሌ በአንድ  ግለሰብ መኖሪያ ቤት መጋዘን ውስጥ ባደረገው ፍተሻ በህገወጥ መንገድ የተከማቸ ተጨማሪ ባለ 20 ሊትር 789 ጀሪካን የምግብ ዘይት ተይዟል።

ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ መሰረት የፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ የፖሊስ አባላት ባከናወኑት የተቀናጀ የክትትል ስራ ዘይቱ መያዙን አስረድተዋል ።

"ለዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ተብሎ በመንግስት ድጎማ ከውጭ ሀገር የገባው ዘይት በህገወጥ መንገድ አከማችቶ ለገበያ ማቅረብ ወንጀል ነው " ያሉት ዋና ሳጅን ደብሩ ህብረተሰቡ ወንጀልን የማጋለጥ ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ያላቸው ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንደ ዋና ሳጂን ደብሩ ገለጻ የፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለውን የምግብ ዘይት ዛሬ ለአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስረክቧል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም