አፍሪካዊያን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመሩት ጥረት ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ተግባር ነው ፡- የተመድ ዋና ፀኃፊ

98

አዲስ አበባ የካቲት 2/2011 የአፍሪካ አገራት የሚገጥሟቸውን ግጭቶችና አለመግባባቶችን በራሳቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የጀመሩት ጥረት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ የመንግስታቱ ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ ተናገሩ። 

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ  የሚገኙት የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዛሬ ከአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ጋር ሆነው መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት ጉቴሬዝ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየው ግጭት በሰላማዊ መንገድ የተፈታ ሲሆን በደቡብ ሱዳን ላለፉት አምስት ዓመታት የተካሄደው የርስ በእርሰ ግጭትም ሰላማዊ እልባት እያገኘ መሆኑን አንስተዋ።  

አፍሪካዊያን እነዚህን የመሳሰሉ ያለመግባባት ችግሮችንና ግጭቶችን በማስወገድ ረገድ እያከናወኑት ያለው አርኣያ የሆነ ተግባር '' ወደ ሌላው የዓለም ክፍል እንደሚስፋፋ ተስፋ አለኝ'' ሲሉ ጉቴሬዘ አክለዋል።

በሚመሩት ድርጅትና በአፍሪካ ኀብረት መካከል በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ትብብር  እንዳለም ጉቴሬዝ አስታሰዋል።   

በዚህ የጋራ ትብብር መሰረት አስካሁን የተከናወኑት ተግባራት በአህጉሪቱ በግጭት አፈታትና መከላከል ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም የተመድ ዋና ፀኃፊ አስረድተዋል። 

ከዚህም ሌላ ከየአፍሪካ ኀብረት ጋር በልማት አጀንዳንና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም ላይ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

''ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ እንዲያውቅልን የምንፈልገው ጉዳይ ብዙ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የልማት ትብብር የሚያስፈገ መሆኑን ነው፤ ያለ ልማት ሰላም የለም'' ብለዋል። 

የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት በበኩላቸው  የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነትና ትግበራ ተፈጻሚነትን እውን ለማድረግ የኀብረቱ አባል አገራት ስምምነቱን በማፅደቅ ወደሥራ እንዲገቡ ጠይቀዋል።  

ለስምምነቱ ተግባራዊነትም አገራት ድንበሮቻቸውን ክፍት ከማድረግ በተጨማሪ  የቪዛ ስርዓትና የሰዎች ነጻ ዝውውርን መፍቀድ እንዳለባቸውም አሳሰበዋል።           

አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር የቀረበውን ስምምነት ፈርመው ከተቀበሉት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሰትሆን በቅርቡም አባል አገራት ወደኢትዮጵያ ሲገቡ የመግቢያ ቪዛ በአየር ማረፊያ ላይ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታም ተግባራዊ አድርጋለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም