የአፍሪካ አጠቃላይ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት በተያዘው የፈረንጆች አመት ወደ 4 በመቶ ያድጋል ተባለ

65

አዲስ አበባ የካቲት 2/2011 የአፍሪካ አጠቃላይ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት በተያዘው የፈረንጆች አመት ወደ4 በመቶ እንደሚያደግ ዓመታዊው የአህጉሪቱ የምጣኔ ኃብት ጠቋሚ ሪፖርት አመለከተ።

በአፍሪካ ልማት ባንክ  በየዓመቱ ይፋ በሚሆነው የምጣኔ ኃብት እድገት ማመላከቻ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፤ በተጠናቀቀው የአውሮፓ ዓመት የአህጉሪቱ አጠቃላይ የምርት እድገት 3 ነጥብ 5 በመቶ ነበር።

በተያዘው ዓመት ግን ይህ አሃዝ ወደ 4 በመቶ የሚያድግ ሲሆን በተከታዩ 2020 ደግሞ 4 ነጥብ 1 በመቶ ይደርሳል ተብሏል።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት እድገትም ከነበረበት 5 ነጥብ 7 ወደ 5 ነጥብ 9 ከፍ እንደሚልም ትናንት በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት ይፋ የሆነው ሪፖርቱ አመልክቷል።

እንዲያም ሆኖ ግን የአህጉሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ለማረጋጋትና ሥራ አጥነተን ለመቆጣጠር የአባል አገራቱ ምጣኔ ኃብት በኢንዱስትሪው የሚመራበትን ፖሊሲ መፍጠር እንዳለበትም ሪፖርቱ መክሯል።

የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ መልሶ መቀነስ ለምጣኔ ኃብቱ እድገት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተመልክቷል። 

ሪፖርቱ ይፋ በሆነበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት ማብራሪያ ምንም እንኳ የአለም ንግድ ውጥረት መሆን፣ የብድር ጫና እና የአለም የፍጆታ እቃዎች ዋጋ መዋዥቅ እንደቀጠለ ቢሆንም የአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት በዚህ መልክ እንደሚያድግ መተንበዩ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ይህን እድገት ለማስቀጠልና እውን ለማድረግ ልማትን በገንዘብ መደገፍን ትኩረት ያደረገና ከብድር ጫና መውጣት የሚያስችል የምጣኔ ኃብት ፖሊሲዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ከአፍሪካ አገራት መንግስታት ይጠበቃል ብለዋል።

እድገቱ በተለይ የወጣቱን የስራ  እድል ፍላጎት በተቀናጀና በወቅቱ ከመፍጠር ጋር  አጣጥሞ ማስኬድ ካልተቻለ በአህጉሪቱ መፃኢ እድል ላይ ትልቅ ተፅኖ እንደሚያሳድርም ነው ያስጠነቀቁት።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን ትብብርና የምጣኔ ኃብት ትስስር ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን አየወሰደች ነው።

በአፍሪካ አገራት መካከል ነጻ የንግድ ልውውጥ ለመፍጠር የቀረበውን አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ፈርመው ከተቀበሉት አገራት መካከል ስትሆን በቅርቡም አባል አገራት ወደኢትዮጵያ ሲገቡ የመግቢያ ቪዛ በአየረ ማረፊያ ላይ ማግኘት የሚችሉበተን ሁኔታም አመቻችታለች።

በአፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግር ለመፍጠርና የምርትና አገልገሎት አብዛህነትን መፍጠር የሚያስፈልግበት ወቅት እየመጣ ነው ያሉት ደግሞ አፍሪካ  ህብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ቪክቶር ሃሪሰን ናቸው።

ይህም እሴትን ለማመንጨት፣ የሥራ አድልን ለመፍጠርና አሀጉራዊውን ነፃ የንግድ ቀጠና ወደተግባር ለመለወጥ የሚያስችል መሆኑንም ፕሮፌሰር ሃሪሰን ገልፀዋል።

የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ወደፊት ተግባራዊ ያደርጉታል ተብሎ በሚጠበቀው ነፃ የንግድ ቀጠና የመጀመሪያ ምእራፍ ትግበራ ከ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን በአገራት መካከል የሚካሄደውን የንግድ ግንኙነትንም በ15 በመቶ እንደሚያሳድገው ሪፖርቱ ጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም