ቡርኪናፋሶ ከኢትዮጵያ የጤና ተቋማት፣ የጤና መዋቅርና የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ልምድ የመቅሰም ፍላጎት አላት

4284

አዲስ አበባ ግንቦት 20/9/2010 ቡርኪናፋሶ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የጤና አወቃቀር ስርዓት እና የጤና ኤክስቴንሽን ስኬትን በመቃኘት ልምድ ለመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ተገለጸ።

የቡርኪናፋሶ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፀሀፊን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ የልኡካን ቡድን በኢትዮጵያ የመስክ ምልከታና የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርግ የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለመቅሰም የመጣው የቡርኪናፋሶ የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የዘርፉን አወቃቀርና የጤና ኤከስቴንሽን መርሃ ግብር በተመለከተ ማብራሪያ ይደረግለታል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡርኪናፋሶ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ በሚኖረው የአምስት ቀናት ቆይታ በአገሪቱ ጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችንና መልካም ተመክሮዎችን ይመለከታል ተብሏል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን እንደተናገሩት፤ በጉብኝት መርሃ ግብሩ መሰረት የሁለቱ አገሮች የጤና ስርዓት አወቀቀርን በሚመለከት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።

የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተቋማትን በሚመለከትም የልምድ ልውውጥ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

የልዑካን ቡድኑ በትግራይ ክልል ተገኝቶ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር አተገባበርን በተመለከ የመስክ ምልከታ እንደሚያካሂድ ተገልጿል።

የቡርኪናፋሶ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፀሀፊ ፍራንሲን ኦድራውጎ መከላከልን መሰረት አድርጎ በተቀረፀ የጤና ፖሊሲ የሚመራው የኢትዮዽያ የጤና ስርዓት አወቃቀር ስኬት ማስመዝገቡ የሚታወቅ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም ለስኬት ያበቃውን ተሞክሮ ወደ ቡርኪናፋሶ በመውሰድ ሥራ ላይ ማዋል የጉብኝታቸው ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።

በሁለቱ አገሮች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መካከል የሚደረገው የመስክ ምልከታና የልምድ ልውውጥ ውይይት ለ 5ቀናት የሚቆይ ነው።