ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለጊኒው ፕሬዚዳንት የእራት ግብዣ አደረጉ

93

አዲስ አበባ  የካቲት 1/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በኢትዮጵያ ጉብኝት ላይ ለሚገኙት የጊኒ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴ የክብር እራት ግብዣ አደረጉላቸው። 

በታላቁ ብሄራዊ ቤተ መንግስት ዛሬ ምሽት በተከናወነው የእራት ግብዣ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሐመትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀኃፊ  ቬራ ሶዊነጌን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

የጊኒው ፕሬዚዳንት ለሶሰት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት ባለፈው ሀሙስ ጥር 29 ቀን 2011 ዓም ነው።

ፕሬዝዳንቱ ባለፉት ሶሰት ቀናት ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በአገራቱ መካከል ያለው ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ላይ መክረዋል።

የአገራቱ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን መመስረቻ ስምምነትም ተፈርሟል።

ስምምነቱን የፈረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና የጊኒው አቻቸው ማማዲ ቱሬ ናቸው።

ቀደም ሲል በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረሙት የሁለትዮሽ ግንኝነት ስምምነትም ተገምግሟል።

አገራቱ ወደፊት በመሪዎች ደረጃ የሚያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ የስትርቴጂክ አጋርነት ስምምነትን ጨምሮ በትምህርት፣ ጤና፣ በግብርና፣ ባህልና ቱሪዝም መስኮች የትብብር ስምምነቶችን ይፈረማሉ ተብሏል።

ኢትዮጵያና ጊኒ በቀድሞ መሪዎቻቸው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና በፕሬዝዳንት ሴኩ ቱሬ አማካኝነት የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ግንባር ቀደምትነት የመሰረቱ አገሮች ናቸው።

አገሮቹ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት በ1950 ዓ.ም ሲሆን ጊኒ ሪፐብሊክ  በ1962 ዓ.ም ኤምበሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷን  መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም