በረሃና ውቅያኖስ የዋጠው ህልም

971

ሰለሞን ተሰራ ኢዜአ

“በህገወጥ ደላሎች የታሰርኩት ገና ሊቢያ ከመግባቴ ነው፡፡ ወደአውሮፓ እንደሚያሻግሩኝ ቃል ገብተው የነበሩት ደላሎች 8 ሺ ዲናር እንድከፍላቸው፤ ካልሆነ ግን እንደሚገሉኝ አስፈራሩኝ፡፡ ሊቢያ እስከገባ ድረስ ያለኝን ገንዘብ በሙሉ ጨርሼ ስለነበር የጠየቁኝን ያክል ገንዘብ ልሰጣቸው አልቻልኩም፡፡ በዚህ ጊዜ ባርያ ሆኜ እንዳገለግል ለአንድ ሰው ሸጡኝ፡፡ የገዛኝ ሰው በተሻለ ትርፍ መልሶ ሊሸጠኝ ሲሞክር እምቢ ብዪ ሳስቸግረው እቤቱ አስሮ አስቀመጠኝ”

ይህ ከ8 አመት በፊት ወደ አውሮፓ ለመግባት ተስፋ ሰንቃ ከኢትዮጵያ  ወጥታ የነበረችው ወጣት ሰበሪ ሀሰን ቃል ነው።  ሰበሪ ሀሰን ሞትን ከሚያስመኝው አሰቃቂ የሊቢያ ቆይታዋ በኋላ አሁን ወደ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡ በተሰበረ ስሜት ታሪኳን መናገሯን ስትቀጥል በባሪያ ንግድ የገዛት ሰው ከቤቱ ካስወጣት በኋላ ለ4 ጊዜያት ያክል በተለያዩ እስር ቤቶች መታሰሯን ገልጻለች፡፡

ሰበሪ የማይረሳ ስቃይን ይዛ በህይወት ተርፋለች። የእርሷ ዓይነት ህልም የነበራቸው ሌሎች አያሌዎች ግን እንደወጡ ቀርተዋል።

ህይወታችንን ለማሻሻል ያስችሉናል ብለው ወደሚያልሟቸው የምእራብ አገራት ህገ-ወጥና አደገኛ በሆነ መንገድ ሲጓዙ ‘ባህር ውስጥ ሰምጠው ቀሩ’ የሚለው የሚዲያ ዘገባ የተለመደ ከሆነ ዓመታት አልፈዋል። በርግጥ በድህነትና ስራ አጥነት ምክንያት የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት የሚታወቅ ቢሆንም፤ የችግሩ መንስኤ ግን ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይደለም።

ምክንያቱም በአገራቸው ሰርተው ጥሪት በማፍራት ህወታቸውን በብቃት መምራት የሚችሉት ሳይቀሩ ልባቸው ወደወጭ ሆኖ ይታያል። ይህንን ህልማቸውን በህጋዊው መንገድ በቪዛና በአውሮፕላን እውን ማድረግ ሲያቅታቸውም ለህገ ወጥ ደላሎች ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል፤ ለማሰብ አንኳ በሚያዳግት አደገኛ በሆነ መንገድ ወደሌላ አገር ለመሄድ ሲሞክሩ ማስተዋሉ የተለመደም ሆኗል። እድል የቀናቻቸው የሚሹት ቦታ በህይወት ሲደርሱ ሌሎች በርካቶች ግን አንደወጡ ይቀራሉ። 

የዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው እ.ኤ.እ በ 2017 ዓ.ም ብቻ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ከ87 ሺ የሚልቁ አፍሪቃውያን ስደተኞች ለሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪ ደላሎች ገንዘብ በመክፈል ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡ አሮጌ መርከቦችን እየተጓዙ የትውልድ ሃገራቸውን ጥለው በየመን አቆራርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ጥረት አድርገዋል። 

አብዛኛዎቹም በሕገወጥ ደላሎች አካላዊ ጥቃት ስቃይ እና ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ገሚሶቹም በሚያሳዘን ሁኔታ የባሕር ውሃው ሲሳይ ሆነዋል።  ያም ሆኖ ዛሬም አደገኛው የባህር ላይ ፍልሰቱ አልቆመም። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ዊልያም ስፒንድለር ሰዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉት ወደው አይደለም ይላሉ።

ከሊቢያ በሜዲትራኒያን ባሕር በሚደረገው አደገኛ ጉዞም በርካታ አፍሪቃውያን ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እየታገቱ የባርነት ሰለባ ሆነው ጉልበታቸው እንደሚበዘበዝ ይታወቃል ::

ኢትዮጵያዊቷ ሰበሪ ሀሰን  እንደሞከረችው ወደአውሮፓ ለመሻገር ሊቢያ የሚገኙት ስደተኞች ህይወት በእጅጉ አሰቃቂ ነው። እስር፣ ግድያና እና የሰውነት አካላቸውን ጭምር በግዳጅ በቀዶ ህክምና እያወጡ የመሸጥ አሰቃቂ ወንጀልም እንደሚፈጸምባቸው በየመገናኛ ብዙኃኑ ተዘግቧል።  የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ስፒንድለር ከሊቢያም አፍሪቃውያን ስደተኞችን የማውጣቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ይናገራሉ።

” ሊቢያ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው :: በስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን ሰቆቃ በጽኑ ስናወግዝ ቆይተናል :: ያ ብቻ ግን አይበቃም :: በሃገሪቱ በእስር እና በባርነት የሚንገላቱ በአስቸኳይ እንዲወጡ ተጨማሪ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን :: በተቻለ ፍጥነት መፍትሄ እንሰጣቸዋለንም ብለን እናምናለን “

በአሁኑ ወቅት ሊቢያ ውስጥ ብቻ ከ400 ሺህ በላይ ስደተኞች እንዳሉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል :: ድርጅቱ በያዝነው የአውሮፓውያን አመት 30 ሺ ያህሉን በፈቃደኝነት መርሃግብር ወደ መጡበት ሀገር የመመለስ ዕቅድ እንዳለውም ታውቋል ::

እኤአ በ2016 ብቻ ከ 5 ሺ በላይ ስደተኞች የሞቱ ሲሆን – አብዛኞቹም ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ ሲሄዱ ሜዲትራንያን ላይ የሞቱ ናቸው፡፡ እኤአ በ2018 ብቻ በሜዲትራንያን ባህር ከ 2 ሺ 200 በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል።

ወደአውሮፓ የሚወስደው መንገድ በተለይ ለሕፃናትና ሴቶች በጣም አደገኛ ነው ይላሉ ጉዞውን የሚያውቁት፡፡ ብዙዎች በጉዞው ላይ ለድብደባ፣ ተገድዶ ለመደፈር፣ ለባርነትና ሌሎች ጥቃቶች ይዳረጋሉ፡፡

ብዙዎች የኤርትራ ሴቶች የሊቢያው ምድረ በዳ ከመሻገራቸው በፊት በሱዳን የፅንስ መከላከያ መርፌ ይወጋሉ። ምክንያቱ ደግሞ በጉዞአቸው ላይ የመደፈር አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጋረጠባቸው ስለሚያውቁ ነው ይላል የአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት መረጃ፡፡

ዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) ከስደት ተመላሾች ማነጋገሩን ጠቅሶ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያውያን አሁንም በሦስት በሮች የሚያደርጉትን ስደት አላቆሙም፡፡

ስደተኞቹ በምስራቅ በር በሚባለው መንገድ በአፋር አድርገው ጀልባ በመሳፈር ወደ የመን ከዚያ ወደ ሳውዲ አረቢያ ይጓዛሉ። ባሳለፍነው ጥር 21 በጅቡቲ በሰጠሙት ሁለት ጀልባዎች ቁጥራቸው ከ50 የሚበልጥ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው እንዳለፈ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ የሚያሳይ ሲሆን 16 ኢትዮያውያንም በህይወት መገኘታቸው ተጠቅሷል።

በደቡብ በር ደግሞ በኬንያ በኩል ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ፣ ማላዊን አቆራርጠው ደቡብ አፍሪካ ለመዝለቅ የሚጓዙት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ ከዚያም የተወሰኑት አሸዋ ይበላቸዋል ወይም በአንዱ አገር እስር ቤት ታጉረው ይቀራሉ፡፡

ነገር ግን አብዛኞቹ ካሰቡበት አገር ሳይደርሱ እንደመሸጋገሪያነት ባረፉበት አገር ተይዘው ለብዝበዛ ፣ ለእስራት፣ ለግዳጅ ሥራ እና ለመታገት ይዳረጋሉ፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚጓዙ፤ እንዲሁም ቀይ ባህርን በጀልባ አቋርጠው የመን ሊገቡ ሲሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚሞቱ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡

ከስደት ተመላሾች

በሊቢያ ምድር ገንዘብ መክፈል ያልቻለ ሰው እጣ ፈንታው ሁለት ነው፡፡ አንደኛው መሞት ሁለተኛው ደግሞ ተሸጦ ጉልበቱን እየገበረ መኖር፡፡ አሁን በሊቢያ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በውል ባይታወቅም ብዙዎች ግን በርካታ ስለመሆናቸው ይስማማሉ፡፡

ስደተኞቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከአለምአቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራው የኢትዮጵያ መንግስት ብዙ ስደተኞችን ወደ አገራቸው በመመለስ በሟቋቋም ስራ ላይ ተጠምዷል፡፡

እነዚህ  ከስደት ተመላሾች አብዛኛውን ገንዘባቸውን ለትራንስፖርት ስለሚያወጡ  ወደ  አገራቸው የሚመጡት  ባዶ እጃቸውን ነው።  ወደ  ሕብረተሰቡ ለመቀላቀል  እርዳታ  የሚያስፈልጋቸው ሲሆን  ይህም  የኑሮ  ሁኔታቸውን  ለማሻሻል  ዕድል  ይፈጥርላቸዋል፡፡

በስደት መንገድ ላይ የነበሩ ስደተኞች  ለመመለስ፣ መልሶ ለማቋቋም ወይም ደግሞ ወደ ነበሩበት ለመመስ የአለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም እገዛ እያደረጉ ነው። 

ጀርመንም ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለመቋቋም የሚያስችል የአራት አመት ፕሮግራም በምስራቅ አፍሪካ ለመተግበር ተዘጋጅታለች።

ከተለያዩ የአፍሪካ  አገራት አውሮፓ ለመድረስ ለሚጓዙ ስደተኞች እኤአ 2018 ከማንኛውም አመት በላይ የከፋ ነበር ተብሎለታል። 

ይህ የሆነበት ምክንያትም በቅርቡ  እየወጣ ያለ ስደተኞችን የሚከለክል ጠንካራ ደንብ እና እየተመረጡ ያሉ ህዝበኛ አመለካከት ያላቸው ፖለቲካዊ ሀይሎች በፈጠሩት ጫና ነው ።

ከዚሁ ጋርም በቅርቡ ጣልያን ስደተኞች ቤት አልባ እና ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ  “ሳልቪኒ ዴክሬ”  የተባለ ፖሊሲ አፅድቃለች። 

እንደነዚህ አይነቶቹ ውሳኔዎች እና ፖሊሲዎች በአጠቃላይ የስደተኞቹን ቁጥር የቀነሰ ቢሆንም የስደተኞች ሞት ግን በንፅፅር ጭማሪ አሳይተዋል።

የተመላሾቹ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በተለይም በዘላቂነት የማቋቋሙ ጉዳይ ፈታኝ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ስለሆነም በርካቶች ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፉ ሁኔታዎች ያስገድዳሉ።

በተለይም መንግሥት ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ፣ የመነሻ ካፒታል በማቅረብ፣ የሙያ ሥልጠና እንዲያገኙ በመደገፍ በአካባቢያቸው ያለውን ሀብት(መሬት፣ ውሃ፣ ጉልበት፣ ውስን ካፒታል) ተጠቅመው እንዲሠሩ እና ግንዛቤያቸውን እንዲያስተካክሉ በማገዝ ሥራ ላይ መተኮር አለበት።

ለእዚህ ደግሞ ፈጣን ፍትሐዊና ግልፅ አገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋት አለበት። በየቦታው ያለው ውጣ ውረድና እንግልት ሊቆም ግድ ነው።

በአንጻሩ ተመላሾቹም ምንም እንኳን መንግሥትና ሕዝብ በሙሉ ደስታ ቢቀበሏቸውና በዘላቂነት ለማቋቋምም ደፋ ቀና እያሉ ቢሆንም ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነው ሊጠብቋቸው እንደማይችሉ ማሰብ ይኖርባቸዋል።

የሀገሪቱን ድህነትና ታዳጊነት ማጤንም ያስፈልጋል። ስለዚህ በአጭሩ ተስፋ የሚቆርጡ መሆንም የለባቸውም። በሁሉም ውስጥ መስረጽ ያለበት አስተሳሰብ ምንም አይነት ችግር ቢኖር ታግለው በማሸነፍ ለራሳቸውም፣ ለቤተሰባቸውም፣ ለሀገራቸውም የሚጠቅሙ መሆን እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ማመንና ለተግባራዊነቱም በዚያው ልክ ሳይታክቱ መስራት ነው።

ከዚህ ባለፈ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን በማስተናገድ በኩል እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ 325 የሚሆኑ የሶማሊያ ተማሪዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስፈላጊው ትብብር ተደርጎላቸዋል።

እ.ኤ.አ. በ2017  በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ 8 ሺ ኤርትራዊን የመጀመሪያ ደረጃ ትምርታቸውን፣ 2 ሺ 200 የሚሆኑ ህጻናት የቅድመ-መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እ.ኤ.አ. እስከ 2016 ድረስ 1ሺ 500 የኤርትራ ስደተኞች በአገራችን የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከዚህም ሌላ 3 ሺ የሚሆኑ ደቡብ ሱዳናዊያን በኢትዮጵያ ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ። ከ900 በላይ ጅቡቲያዊያን በኢትዮጵያ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የነጻ የትምህርት እድል አግኝተዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጎረቤት አገር ስደተኞችን አቅፋና ደግፋ መኖሯ ሞልቷትና ተርፏት ሳይሆን የረዥም ጊዜ ትብብር ሁልጊዜም በህዝብ ልብና አዕምሮ ተቀርጾ የሚኖር መሆኑን ስለምታውቅ ነው።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚከ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ በዘንድሮው የህብረቱ ጉባኤ መክፈቻ ላይ በአፍሪካ አሁን ላይ 14 ነጥብ 7 ሚሊየን ተፋናቃዮች እና 7 ነጥብ 3 ሚሊየን ያህል ስደተኞች አሉ ብለዋል።

ከነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ተፋናቃዮችና ስደተኞች የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዜጎች መሆናቸውንና ተፈናቃዮቹ 59 በመቶ እንዲሁም ስደተኞች 49 በመቶውን ድርሻ መያዛቸውን አረጋግጠዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ 900 ሺ የሚሆኑ ስደተኞችን ያስጠጋች ሲሆን ከነዚህ መካከል የሶማሊያ 245 ሺ ፣ ደቡብ ሱዳን 349 ሺ ፣ ኤርትራ 167 ሺ ፣ ሱዳን 41 ሺ ፣ የመን 1 ሺ 200 እና የሌሎች የጎረቤት አገራት 6 ሺ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ናች።

ተፈናቃዮች

በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገር ውስጥ የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀቡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ የድርጅቱ የህፃናት ፈንድ እንዳስታወቀው በአገር ውስጥ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ደርሶ ነበር፡፡

በአገሪቱ 1ነጥብ 6 ሚሊዮን የነበረው የተፈናቃዮቹ ቁጥር በ1ነጥብ 2 ሚሊዮን ጨምሮ የእርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጎታል ሲል በነሃሴ 2010 ዓም የወጣው የመንግስታቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ኦሮሚያ፣ ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ተፈናቃዮቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ድረቅን ጨምሮ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለችግር የሚዳረጉ ወገኖችን ማየት የተለመደ ቢሆንም፣ በግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የሰው እጅ ማየታቸው ግን እንግዳ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስተው የነበሩ ገጭቶቸን ተከትሎ በርካቶች ተፈናቅለው ነበር።

አንዲያም ሆኖ  ከህብረተሰቡ ጋር በተቀናጀ መንገድ በተከናወነው ተግባር ከአንድ ሚሊዮን የሚለቁ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን ሰሞኑን የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ይፋ አድርገዋል።

ሚኒስቴሩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ቀሪ ተፈናቃዮችን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሙሉ በሙሉ የማቋቋም ስራ እንደሚያከናውንም ተናግረዋል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በግጭት ሳቢያ ከተፈናቀሉባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል የሶማሊያ – ኦሮምያ አዋሳኝ ድንበር፣ ደቡብ ክልል፣ ቤኒሻንጉል፣ ሞያሌ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

እንደተባበሩት መንግስታት ሪፖርትም፤ ባለፉት 2 ዓመታት በአገር ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ከተፈናቀለባቸው አገራት ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ትመደባለች። 

በአዲስ አበባ የተጀመረው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም ስደት፣ ከስደት ተመላሾችና መፈናቀል መነጋገሪያ አጀንዳዎቹ ናቸው።   መሪዎቹ እነዚህን ለአደጋ የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ለማቋቋም፤ ብሎም የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ የሚያግዝ ውሳኔ ያሳልፋሉ ብለን እንጠብቅ።