ዩኒቨርሲቲው በ12 ሚሊዮን ብር የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮች እያካሄደ ነው

88
ደብረብርሃን ግንቦት 20/2010 ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት ለጥናትና ምርምር ሥራ 12 ሚሊዮን ብር በመመደብ የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው 5ኛ ዓለም ዓቀፋ የምርምር ሲፖዚየም ትናንት ሲጀመር (በዩኒቨርሲቲው) የተቋሙ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የአካበቢውን ህዝብ መሰረታዊ ችግሮች በመለየት በጥናትና ምርምር ለመፍታት ሲሰራ ቆይቷል። "ባለፉት 10 ዓመታት ከተካሄዱ ማህበረሰብ ተኮር የጥናትና ምርምር ሥራዎች መካከል 520ው ተጠናቀው የተወሰኑ የምርምር ውጤቶች ወደ ማህበረሰቡ ወርደው በመተግበር ላይ ናቸው" ብለዋል። በወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ በጓሮ አትክልት፣ በቢራ ገብስ፣ በአሳ አርባታ፣ በዶሮ እርባታና በዳቦና ማካሮኒ ስንዴ ዝርያ ማሻሻል ላይ የተካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን የምርታማነት ችግሮች የሚፈቱ በመሆናቸው ውጤቶቹ ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸውን ነው የገለጹት። በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው በደቡበ ክልል በሲዳማ ዞን የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ጥናትና ምርምር እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። የምርምር ዘርፉን በተደራጀ አግባብ ለመምራት እንዲቻልም የምርምር ሀሳብ ማበልጸጊያ ማዕከል በዩኒቨርሲቲው ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱን ዶክተር አልማዝ ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው  ቀደም ሲል ተጀምረው በሂደት ላይ ያሉ እንዲሁም የተጠናቀቁ 54 የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በዚህ ዓመት ወደ ትግበራ ለማስገባት 12 ሚሊዮን ብር መመደቡንም  አስታውቀዋል። ያለፉት አራት ሲፖዚየሞች የእውቀት ሽግግር የተደረገበት፣ በጋራ የመስራት አመለካከቶች የዳበሩበት መሆኑን ፕሬዚዳንቷ አመልከተው፣ በዚህ አመት በተበታተነ መልክ ይካሄድ የነበረን የምርምር ሥራ በቅንጅት እንዲካሄድ መደረጉን ገልጸዋል ። የሲምፖዚየሙ  ዓላማም ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ዘርፍ የሰራቸውን ለአጋር አካላትና ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ከሌሎችም ልምድና እውቀት ለመቅሰም እንደሚያስችለው አመልክተዋል። በሲምፖዚየሙ የተካሄዱ 60 የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበው ተጨማሪ ግብአት የሚሰበሰብባቸው እንደሆነም አስረድተዋል። እንደፕሬዚዳንቷ ገለጻ፣ የሚቀርቡት የጥናትና የምርምር ጽሁፎች በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በምህንድስናና በሌሎችም ዘርፎች ያተኮሩ ናቸው። ከእዚህ በተጨማሪ በሲምፖዚየሙ ላይ ከጀርመንና ከአሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ አራት ተመራማሪዎች የምርምር ዕሁፋቸውን በሲምፖዚየሙ ላይ አቅርበዋል። በመድረኩ ላይ በምርምር ያገኘውን አንድ ጄነሬተር ለዕይታ ያቀረበው  በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል መህንድስና 5ኛ ዓመት ተማሪ አበበ መንግስቱ በበኩሉ፣ ጀነሬተሩ የአካባቢ ብክለትን የሚከላከል፣ ነዳጅ የማይጠቀምና በመኪና ባትሪ ብቻ የሚሰራ መሆኑ አመልክቷል። በምርምር ሲምፖዚየሙ ላይ ከትምህርትና ከምርምር ባለሙያዎች በተጨማሪ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የወረዳና የዞን አመራሮችም ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም