አምርቶ መሸጥ ወይስ ሸጦ ማምረት ? - ኢዜአ አማርኛ
አምርቶ መሸጥ ወይስ ሸጦ ማምረት ?

ገብረህይወት ካህሳይ /ኢዜአ/ ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ አርሰናል ። ያረስነው መሬት ግን ጥቂቱን ብቻ ነው ። በሔክታር የምናገኘው ምርትም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ። ለምን ? አገራችን በዓመት ውስጥ ሶስት ወቅቶችን ታስተናግዳለች ። እነሱም በጋ ፣ በልግና የክረምት ወቅቶች ናቸው ። በበልግና በክረምት ወቅቶች በቂ የዝናብ መጠን ታገኛለች ። ዓመት ከዓመት የሚፈሱ ወንዞች ባለቤትም ናት ። በከርሰ ምድር ውሃም ጭምር የታደለች አገር ናት - ኢትዮጵያ ። 74 ሚሊዮን ሔክታር የሚታረስ መሬት ያለን ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ያረስነው የመሬት መጠን 13 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ ነው ። እሱም ቢሆን በአብዛኛው ብዙ ህዝብ ተጣብቦ በሚኖርበት በደጋውና በወይናደጋው አካባቢ የሚከናወን እርሻ ነው ። በተበጣጠሰ መልኩ በገበሬ ማሳ ላይ በበሬ የሚታረሰው መሬት በሔክታር የሚሰጠው ምርት አናሳ በመሆኑ የገበያ ፍላጎታችንን ማሟላት ይቅርና የምግብ ዋስትናችን ለማረጋገጥ እንኳን ፈታኝ አድርጎታል ። ምክንያቱም ግብርናችን ገና ኋላ ቀር ነው ። ማዳበሪያ የሚጠቀመው አርሶአደራችን ቁጥር 62 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው ። የምርጥ ዘር አቅርቦታችን 25 በመቶ ፣ የመካናይዜሽን አጠቃቀማችን ገና 6 በመቶ ፣ በመስመር የመዝራት ባህላችን 28 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ። በበሬ ታርሶ በዘር ከተሸፈነው መሬት የሚገኘውን ምርት ለመሰብሰብ በሚደረገው እንቅስቃሴም አጨዳው የሚከናወነው 88 በመቶ በእጅ ነው ። ውቂያው ደግሞ 91 በመቶ የሚሆነው ከብቶች በማዞር የሚከናወን ነው ። ይህንኑ ተከትሎ ደግሞ ከአጠቃላይ ምርታችን 25 በመቶ የሚሆነው በምርትና በድህረ ምርት ወቅት ይባክናል ። ግብፅ ከእኛው የሚሄደውን ውሃና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ በመጠቀም በደረቃማ መሬት ላይ በሔክታር 345 ኩንታል በቆሎ ማምረት ስትችል ለም መሬት ባለው የጋምቤላ ክልል የሚገኘው አማካይ የበቆሎ ምርት ግን 17 ኩንታል ብቻ ነው ። እስራኤል በመስኖ ልማት ከአንድ ሔክታር መሬት 3 ሺህ ኩንታል ቲማቲም የምታመርትበት ደረጃ ላይ ደርሳለች ። የእኛው አማካይ ምርት ግን ገና ከ350 እስከ 400 ኩንታል ባለው መሀል ይገኛል ። ችግሮቹ በሙሉ የሚያመላክቱት ግብርናችን መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ነው ። ለግብርናው ትራንስፎርሜሽን ደግሞ መስኖን ማእከል ያደረገ የግብአት ፣ የመካናይዜሽንና የባለሙያዎች እውቀትና ታታሪነት መገንባት የግድ ይላል ። ችግሮችን የምናነሳው የበለጠ ማደግ እንደምንችል ለማመላከት እንጂ ሂደታችን በሙሉ ጨለማ አድርጎ ለማሳየት አይደለም ። ተስፋ ሰጪ ጅምሮችና ውጤቶችም ታይተዋል ። በጅምር ቢሆንም በነቀምቴ አካባቢ በሔክታር 100 ኩንታል በቆሎ ማምረት ተችሏል ። ራያ አካባቢ በሔክታር 1 ሺህ ኩንታል ቲማቲም የተገኘበት አጋጣሚም አለ ። በአፋር በሔክታር 35 ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ስንዴ እየተመረተ ነው ። በኢትዮ ሶማሌ ጎዴ አካባቢ በሔክታር 45 ኩንታል ምርጥ የሩዝ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ ያስረዳሉ ። ከ100 ሚሊዮን ኩንታል ያልዘለለ የነበረው ዓመታዊ የግብርና ምርታችን አሁን ላይ ከ300 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መድረሱም አገራችን ባለ ብሩህ ተስፋ መሆንዋን አመላካች ነው ። አስፈላጊውን ቴክኖሎጂና ግብአት ተጠቅመን ምርታማነታችን በሶስት እጥፍ ብቻ ማሳደግ ብንችል እንኳን በዓመት 1 ቢሊዮን ኩንታል ማምረት እንደምንችል ዶክተር ኢያሱ ይናገራሉ ። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ መንግስት በአንድ በኩል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ በሌላ በኩል ደግሞ ለሰፋፊ እርሻዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰነባብቷል ። የሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፉ ግን በበርካታ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ የታሰበውን ያክል ውጤት አልታየበትም ። ችግሩን ለይቶ መፍትሔ በማስቀመጥ ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ደግሞ አንድ ዓመት የፈጀ የዳሰሳ ጥናት ተካሔዷል ። ጥናቱን ያካሔደው የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ነው ። በሚኒስቴር መዓረግ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ እንደገለፁት በተለያዩ ክልሎች ለሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት 3ነጥብ 1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ተለይቶ 2 ሚሊዮን ሔክታር ለባለሃብቶች ተላልፎ ነበር ። ዘርፉ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ በተጨባጭ የለማው ግን 800 ሺህ ሔክታር መሬት ብቻ ነው ። ከዚህ የሚገኘው ዓመታዊ አማካይ ምርት ደግሞ ከ10 ሚሊዮን ኩንታል የዘለለ አይደለም ። በጥናቱ የተለዩ የዘርፉ ማነቆዎች በዝርዝር ያቀረቡት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት እንዳሉት አዳዲስ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ አልሚዎች የተሳለጠ የመሬት አቅርቦት ያለማመቻቸት ፣ ለኢንቨስትመንት የተላለፉ መሬቶችን በተሟላ ሁኔታ ወደ ልማት ማስገባት አለመቻልና የእርሻ ኢንቨስትመንት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ለልማት ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር ከችግሮቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው ። የአልሚዎቹ ምርትና ምርታማነት ዝቅተኛ መሆን ፣ ዘላቂ የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት ማእከል ያደረገ ልማት አለማካሄድና አስፈላጊው የገበያ ትስስር በመፍጠር የሎጅስቲክ አገልግሎት እንዲሟላ አለማድረግና ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት አለመዘርጋትም የዘርፉ ችግሮች ናቸው ብለዋል ። ዘርፉን መንግስትና በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት በሚገባ አለመደገፋቸው እንዳለ ሆኖ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚፈጥሩዋቸው ችግሮችም በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተፈትሿል ። የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው አናሳ በመሆኑ በሄክታር የሚያገኙት ምርት በአርሶአደር ማሳ ላይ ከሚገኘው ምርት ጋር ሲነፃፀር ብዙም ፈቀቅ ያለ አለመሆኑን ፣ በመንግስት የሚሰጠው ማበረታቻ ለታለመለት ዓላማ አለማዋልና የተሰጠውን መሬት ለ3ኛ ወገን አሳልፎ መስጠት ጭምር የሚገለፁ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካካትና ተግባር ይስተዋላሉ ነው የተባለው ። ዘርፉ እነዚህን ችግሮች በመፍታት አሁን እየለማ ካለው መሬት ብቻ በዓመት በአማካይ 60 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ይቻላል ። የተለየው መሬት ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት ማስገባት ከተቻለ ደግሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ኩንታል የማምረት አቅም እንዳለው አቶ ያዕቆብ ያላ ተናግረዋል ። በጋምቤላ ክልል 500 ሔክታር መሬት በማልማት ተግባር ላይ የተሰማሩ አቶ እኩች ኡጉል ኡኬሎ በሰጡት አስተያየት አገራችን ተወረረች ሲባል ጠብመንጃ አንስተን በአንድነት እንደምንዋጋ ሁሉ በፀረ ድህነት ትግሉም እጅ ለእጅ ተያይዘን ከተረባረብን ውጤታማ እንሆናለን የሚል ተስፋ አላቸው ። የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት መስፋፋት አገራዊ የኢንዱስትሪ ግብአት ፍላጎት ለማሟላት ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅማችን ለማሳደግና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ወሳኝ ሲሆን ለግብርናችን መዋቅራዊ ሽግግርም ፋይዳው የጎላ ነው ። የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ከተቻለ ደግሞ ከሁሉም በላይ የተትረፈረፈ ምርት በማምረት የምግብና የስነ ምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ እንችላለን ። ከዚህ ባሻገር የውጭ ምንዛሪ አቅማችን ለማጎልበትና ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ገበያን ማእከል ያደረገ የአመራረት ዘዴ መከተል ያስፈልጋል ። አምርተን ገበያ ፍለጋ መንከራተት ሳይሆን “ ሸጠን ማምረት “ መልመድ አለብን ። አምርቶ መሸጥ ሳይሆን ” ሸጦ ማምረት “ አለብን የምንልበት ምክንያት የአገራችን የግብርና ምርቶች ተፈጥሮአዊ ይዘታቸው የጠበቁ (organic) በመሆናቸው በዓለም ገበያ በተለይ ደግሞ በአውሮፓ በእጅጉ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጥቷል ። ዋናው ችግር የገበያ መታጣት ሳይሆን በሚፈልጉት ዓይነት ፣ ጥራትና ብዛት አምርተን ማቅረብ አለመቻላችን ነው ። ስለዚህ ምን ዓይነት ምርት ? ለየትኛው ገበያ ? በምን ዓይነት ዋጋ ? በየትኛው የጥራት ደረጃ ? ምን ያክል ቶን ? የሚለውን በጥናት በመለየት ወደ ማምረት የምንገባ ከሆነ “ ሸጦ ማምረት “ ይቻላል ማለት ነው ።