በህብረተሰቡና መንግስት ትብብር የተገነባው የሰላድንጋይ ቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ኮሌጅ ተመረቀ

78
ደብረብርሃን ግንቦት 20/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ  ውስጥ በህብረተሰቡና መንግስት ትብብር  የተገነባው የሰላድንጋይ ቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ኮሌጅ ተመረቀ። ተቋሙን ለመገንባት  18 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር ወጪ ተደርጓል። የአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ክብረት በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም  ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ይህንኑ መሰረት በማድረግም የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትን በማስፋፋት ኢንዱስትሪውን የሚደግፉና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጥረቱ እንደሚቀጥል  ገልፀዋል። እስካሁን በተደረገ ጥረት ለአነስተኛና መካከለኛ  ፋብሪካዎች የሚሆኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ያለባቸውን የባለሙያ እጥረት መፍታት መቻሉን ገልጸዋል። በእነዚህ ኮሌጆች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ተማሪዎች በተጨማሪ አርሶ አደሩ፣ የመንግስት ሰራተኛውና ሌላውም ህብረተሰብ አጋጣሚውን በመጠቀም በትርፍ ጊዜያቸው  ስልጠናዎችን በመውሰድ ተጨማሪ ስራ ፈጣሪ መሆን እንደሚችሉም አስረድተዋል።፡ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝም ለአዲሱ ኮሌጁ አስፈላጊ ማሽኖችንና ግብዓቶችን ለማሟላት መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል፡፡ የሞጃና ወደራ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ንጉሴ ብርሃኑ ኮሌጁ እንዲከፈት ህብረተሰቡ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ መንግስት በሰጠው በጎ ምላሽም ግንባታው በ2008 ዓ.ም መጀመሩን ገልፀው የግንባታውን ወጪ ህብረተሰቡና መንግስት በጋራ መሸፈናቸውን ተናግረዋል። በ11 ሄክታር መሬት ላይ በ18 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር ወጭ የተገነባው ይኸው  ኮሌጅ በውስጡ የመማሪያ ክፍል ፣ የማሰልጠኛ ወርክሾፖችና የአስተዳደር ህንፃዎችን ያካተተ ነው። ኮሌጁ አሁን ላይ 280 ሰልጣኞችን ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን በቀጣይ ዓመት ከ500 በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሞጃና ወደራ ወረዳ የብርቃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማ ሀይለማሪያም ከዚህ በፊት ሁለት ልጆቻቸውን ደብረብርሃን ሲያስተምሯቸው  ከወጭው በላይ ለእንግልት መዳረጋቸውን ጠቆመዋል። በተጨማሪም አርሶአደሩን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ''ሴት ልጆቻቸው ለተለያዩ ጥቃት ይጋለጣሉ''  በሚል ሩቅ ስፍራ ልከው እንደማያስተምሩ ተናግረዋል፡፡ አሁን ኮሌጁ በአቅራቢያቸው በመከፈቱ ያለቻቸውን አንድ ሴት ልጅ እያስተማሩ በትርፍ ጊዜዋም በስራ እንደምታገዛቸው አርሶ አደር ግርማ ገልጸዋል፡፡ ተማሪ ሀይለስላሴ አይፎክሩ በበኩሉ የሚረዳዉ ቤተሰብ ባለመኖሩ በ2006 የ10ኛ ክፍል አጠናቆ በቀን ስራ ሲተዳደር እንደነበር ገልፆ አሁን በኮሌጁ አይሲቲ እየተማረ በትርፍ ጊዜው በመስራት ራሱን እየደጎመ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ ትናንት በተካሄደው የምርቃ ስነስርዓት ላይ የክልል፣ የዞንና የአጎራባች ወረዳ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ባለሀብቶችና በወረዳው ከ15ቱም ቀበሌ የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም