በአዲስ አበባ 10 ወረዳዎች 14 ሺህ አባወራና እማወራ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል ሆነዋል

1939

አዲስ አበባ ግንቦት 20/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በአሁኑ ወቅት በሙከራ ደረጃ እያካሄደ ያለውን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሽፋን መርሃ ግብር ለማስፋፋት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ።

ካለፈው ታህሳስ ወር 2010 ዓ ም ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው በዚህ መርሃ ግብር 14ሺህ የሚሆኑ የከተማው አባወራዎችና እማወራዎች አባል በመሆን ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸው ተገልጿል።

ቢሮው ከአስተዳደሩ አመራሮችና የካቢኔ አባላት እንደዚሁም ከሆስፒታሎች፣ ከጤና ጣቢያዎች፣ ከማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የቦርድ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ታደሰ አጥላባቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፍትሃዊና ተደራሽ የጤና አገልግሎትን በአዲስ አበባ  ለማስፋፋት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

ከዚህ አኳያ ዜጎች በአነስተኛ ወጪ አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሽፋንን ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከታህሳስ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ ደረጃ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሽፋን መርሃ ግብር በ10 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኃላፊው በዚህም 14ሺ የሚሆኑ አባወራዎች አገልግሎቱን ለማግኘት አባል መሆናቸውን አስታውቀዋል።

አገልግሎቱን ወደሌሎች የከተማው ክፍሎች በማስፋፋትም ህብረተሰቡን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ቢሮው በአሁኑ ወቅት በ10 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ የተጀመረውን የጤና መድህን አገልግሎት ወደ 20 ተጨማሪ ወረዳዎች በማስፋት ህብረተሰቡ የተቀናጀና የተሻለ አገልግሎት የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ስለአገልግሎቱ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግን ጨምሮ  ተጠቃሚውን መመዝገብ፣ መታወቂያ መስጠትና ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኋላ በመጪው ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መርሃ ግብር ተግባራዊ እንደሚደረግባቸው ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው በጤና መድህን መርሃ ግብር አማካኝነት የጤና አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች መልካም የሚባሉ ቢሆንም የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

ታካሚዎች በጤና ተቋማት እንግልት ሳይደርስባቸው ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠትና ከሌሎች ጋር በቅንጅት በመስራት የመርሃ ግብሩን  ውጤታማነት ለማረጋገጥ መትጋት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የውይይቱ ታዳሚዎች በበኩላቸው የህክምና መሳሪያና የመድሃኒት እጥረት የጤና መድህን አባላት ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ እንዳይሰጡ እክል እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱን የተቀላጠፈ ለማድረግ አስፈላጊ ግብአቶችን የማሟላት ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ አሳሰበዋል።