የኢንዱስትሪ ግብዓት እጥረትና ጥራት ችግር ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያሳጣት ነው

972

አዲስ አበባ ጥር 30/2011 አምራች ኢንዱስትሪዎች እየገጠማቸው ያለው የግብዓት አቅርቦትና የጥራት ችግር ምርታማነታቸውን እንዳያሳድጉ ማነቆ እንደሆነባቸው ገለፁ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ሥራ በማጠናከር የዘርፉን ምርታማነት ማሳደገ ይቻል ዘንድ የጥሬ እቃ ግብኣትንና ፋይናንስን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርገው መንግስታዊው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ነው።

ድርጅቱ በዚሁ ተግባሩ ዙሪያ ባሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ለመምከር ዛሬ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በዚሁ ወቅት የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለፁት የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት እጥረትና ጥራት ችግር ዘርፉ በሚገባው መጠን እንዳያድግ እንቅፋት እየሆነ ነው።  ይህንን ችግር ለመፍታት ድርጅቱ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከሞጆ ቆዳ ፋብሪካ የመጡት አቶ ሬድማን በዳዳ  እንዳሉት ድርጅቱ በዘርፉ ላሉ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ቢያደርግም በተለይ ቆዳን ለማቀነባበር የሚያሰፈልገውን ጨው በጥራትና በበቂ መጠን ማቅረብ ላይ እጥረት ይስተዋልበታል።

የግብኣት አቅርቦትና ጥራት መጓደል ደግሞ በቆዳው ምርት ጥራት ላይ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ አቅርቦቱ አስተማማኝ የሆነና ጥራቱን የጠበቀ ጨው ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ ከድርጅቱ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር ዋና ፀሀፊ አቶ አጋአዚ ገብረየሱስ በበኩላቸው የጥጥ ምርት አቅርቦት ላይ  የጥራት  ችግር እንዳለ ገልፀዋል።

ማህበሩም ችግሩን ለመፍታት ከጥጥ አምራቾችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አልሚ ምግብ አምራች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃኑ ሞሲሳ ደግሞ የድርጅቱ አቅም ከተሰጠው ተልዕኮ ጋር ሲነፃፀር አይመጣጠንም ይላሉ።

ዶክተር ብርሃኑ “ድርጅቱ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን ዘርፎችን ለይቶ በውስን ዘርፎች ላተ ትኩረት ሰጥቶ መሰማራት አለበት” ባይ ናቸው።

አስተያየት ሰጪዎቹ ድርጅቱ የሚስተዋልበትን ቢሮክራሲያዊ አሰራር በዘመናዊ አደረጃጀትና አሰራር መቀየር እንዳለበትም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ በበኩላቸው በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ኩንታል ጨው ቢኖርም ድርጅቱ ማቅረብ የቻለው  ግን 52 ሺህ ኩንታል ብቻ መሆኑን ገልፀዋል።

በአፋር ክልል በጨው አቅርቦት ላይ የሚስተዋለው የአሰራር ችግር ከተፈታ  ድርጅቱ 1 ሚሊዮን ኩንታል የመግዛት አቅም እንዳለው ነወ ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት።

ለችግሩ መፈታት ድርጅቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም አንሰተዋል።

ድርጅቱ የሚገዛቸው ግብዓቶች ጥራታቸው በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ወንዳለ የጥራት ጉድለት ከተገኘ ተፈትሾ እንደሚመለስ ይደረጋል በለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 36 ሚሊዮን ብር በመመደብ  ከ94 ሺ ኩንታል በላይ  የኢንዱስትሪ ጨው ለማቅረብ አቅዶ ማቅረብ የቻለው ግን ግማሽ ያህሉን ብቻ መሆኑን ገልፀዋል።

ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የሚውል ከ4 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ   የተዳመጠ ጥጥ በ195 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማቅረብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ይህም ሊሳካ አንዳልቻለ ገልፀዋል።

ድርጅቱ በ85 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶቹ ካሉ ሰራተኞቹ ጋር መወያየቱንና በቀጣይ የተነሱ  የአሰራር ቅልጥፍና ችግሮች እንደሚፈቱ  ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪዎች የቢሮክራሲ ችግር ሲገጥማቸው ማሳወቅ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ድርጅቱ የካፒታል አቅሙን በማሳደግ የተነሱ የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም አብራርተዋል።