የመጀመሪያው አገር አቀፍ የውሹ ውድድር (ሳንሹ ካፕ) ፍጻሜውን አግኝቷል

672

አዲስ አበባ 30/2011 የመጀመሪያው አገር አቀፍ የውሹ የግል የበላይነት የነጻ ፍልሚያ ውድድር (ሳንሹ ካፕ) ዛሬ ፍጻሜውን አገኘ።

ውድድሩ ከጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የተካሄደ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 70 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።

ውድድሩ “ሳንሹ ካፕ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የስፖርቱ መጀመሪያ ከሆነችው ቻይና የተገኘ ቃል እንደሆነና ቃሉም ሲተረጎም ነጻ ፍልሚያ የሚል ስለሆነ ነው።

በወንዶች ከ48 እስከ 52 ፣ ከ53 እስከ 56 ፣ ከ57 እስከ 60 እና ከ61 እስከ 65 ኪሎ ግራም እንዲሁም በሴቶች ከ48 እስከ 52 ኪሎ ግራም እና ከ53 እስከ 56 ኪሎ ግራም የክብደት ዘርፎች (ካታጎሪ) የግል የበላይነት የተካሄደባቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ዳኜ ለኢዜአ እንደገለጹት በውድድሩ መዝጊያ ቀን በሁሉም የክብደት ዘርፎች የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

በሁሉም የክብደት ዘርፎች ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት ያገኙ ሲሆን እንደየቅደም ተከተላቸው የ5፣ 3 እና 2 ሺህ ብር ሽልማት እንዳገኙም ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ለአምስት ቀናት የተካሄደው ውድድር ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበትና የስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት ነበርም ብለዋል።

ውድድሩ የመገናኛ ብዙሃንን በቂ ሽፋን ባለማግኘቱ የተመልካች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ እንደ ድክመት የሚታይና በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ያለውን ድክመት ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የውድድሩ አላማ  የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንዲሁም ከሌሎቹ የማርሻል ስፖርቶች የሚለይበትን ነገር ለማሳየት እንደሆነም ነው አቶ ዳኜ ያስረዱት።

በተያዘው በጀት ዓመት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አገር አቀፍ የውሹ የአርት (ጥበብ) ውድድር ለማካሄድ እቅድ እንዳለውና ለዚህም ይረዳው ዘንድ ስፖንሰሮችን የማፈላለግ ተግባር እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ከውድድሮቹ በተጨማሪ በስፖርቱ ብቁ ባለሙያዎች እንዲፈሩ በማሰብ ዓለም አቀፍ ስልጠና በኢትዮጵያ እንዲሰጥ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ሶስት የውሹ ስፖርተኞች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ቻይና ሄደው ለስድስት ወር ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለተወዳዳሪዎቹ የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል።