በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ውይይት ላይ እንዳይሳተፉ ተጠየቀ

60

አዲስ አበባ ጥር 30/2011 በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው ውይይቶች ላይ እንዳይሳተፉ አንዳንድ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጠየቁ።

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ከቦርዱ ሪፎርም ጋር ተያይዞ የፓርቲዎች የምዝገባ ህግ እስኪሻሻል ፓርቲዎቹ በውይይት መሳተፋቸውን ይቀጥላሉ ብሏል።

103 አገር አቀፍ፣ ክልላዊና ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ትናንት ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።

አመራሮቹ  በፓርቲዎች መካከል የሚኖረው ግንኙነትና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሰራር ስርዓት ቃል ኪዳን ላይ ነበር ውይይት ያደረጉት።

በሰነዱ ክፍል አንድ ጠቅላላ ድንጋጌ ላይ እንደተቀመጠው የፖለቲካ ፓርቲ ማለት በአገር አቀፍ ወይም በክልል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ በዴሞክራሲ ስርዓት የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ በህግ አግባብ የተመዘገበ ወይም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያስፈጽመው የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሰረት ቦርዱ በሚያስቀምጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በፓርቲነት ለመመዝገብ በሂደት ላይ ያለ ድርጅት ነው።

ይሁንና በውይይቱ እየተሳተፉ ያሉት አገር አቀፍ፣ ክልላዊና በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

በመሆኑን በሰነዱ ላይ በተቀመጠው መሰረት በፓርቲነት የተመዘገበ ወይም ለመመዝገብ በሂደት ላይ ያለ ፓርቲ ብቻ በውይይቱ መሳተፍ እንዳለበት ነው አንዳንድ አገር አቀፍ ፓርቲ አመራሮች ያነሱት።

ይሁንና ገዥው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ተወካይና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች ከውጭ አገር የመጡ ፓርቲዎች በውይይት እንዳይሳተፉ ማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ማጥበብ መሆኑን ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳም ፓርቲዎቹ የሚመዘገቡበት የጊዜ ገደብ የሚወሰነው በፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሻሻል ላይ ተመስርቶ ነው ብለዋል።

በመሆኑን በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ላይ የተመዘገቡም፤ ያልተመዘገቡም ፓርቲዎች መሳተፋቸው የማይቀር መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም