የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ወንጀል የፈጸሙ አባላቱን ያለመከሰስ መብት በሙሉ ድምፅ አጸደቀ

62

ጅግጅጋ ጥር 30/2011 የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀሎች የተጠረጠሩ የ12 የምክር ቤት አባላቱን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።

ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳባቸው አባላት በፍርድ ቤት ክስ እንደሚሰረትባቸው የክልሉ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ያለመከሰስ መብታቸውን ካነሳባቸው መካከል የቀድሞው የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢሶሕዴፓ) ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መሐመድ ረሺድ ኢሳቅ፣የቀድሞዋ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሱዓድ አህመድና የቀድሞዋ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ማጂዳ መሐሙድ ይገኙበታል።

የቀድሞዎቹ  የክልሉ የውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊና የኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈርቱን አብዲ፣የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አብዲ ፣የክልሉ ንግድ፣ ትራንስፖርትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር አብዲ ፣ የእንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ መሐዲ በምክር ቤቱ  ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳባቸው መካከል ናቸው።

እንዲሁም የቀድሞዎቹ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ቢሌ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሙድ አህመድ፣የክልሉ ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ  አቶ አብዲሐሊም መሐመድ፣የክልሉ ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቲ ሰብሳቢ ወይዘሮ ነስራ ሐሰንና የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አያን ሹክሪ በጉባዔው ያለመከሰሰስ መብታቸው እንዲነሳ ተደርጓል።

የክልሉ ዐቃቤ ሕግ አቶ አብዲ ወሊ በዚሁ ወቅት አባላቱ በሰኔና ሐምሌ 2010 በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ፣ አለመረጋጋት በመፍጠርና በሕዝብ ሀብት ላይ ከሙስና በመፈፀም በእስር ላይ ከሚገኙት የቀድሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር በግብረ አበርነት መሥራታቸውን ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ክስ እንደሚመሰርትባቸው አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ በአባላቱ ላይ  የቀረበውን ያለመከሰስ መብት በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት በሚያካሄደው ጉባዔ በክልሉ መንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ይወያያል።

የክልሉ ዋና ኦዲት ቢሮ እንደገና ለማቋቋም ረቂቅ ዓዋጅ በመመርመር ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመርና የ47 የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናትና ግለሰቦች ጉዳይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም