የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ ነው

903

አዲሰ አበባ ጥር 30/2011 በኢትዮጵያ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።

የቅዱሰ  ጴጥሮሰ ስፔሻላይዝድ ሆሰፒታል የጤናማ እናትነትን ወር በማስመልከት የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም  በዚህ ወቅት እንደገለጹት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል።

በሆስፒታል ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር ዝቅተኛ መሆንና  የጤና አገልግሎት ጥራት መጓደል ለእናቶች ሞት መጨመር አይነተኛ መንስዔ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ፣ የጤናው ሴክተር ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲያደርግ በሚኒስቴሩ በኩል ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ዶክተር መሠረት ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በዚሁ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት፣ ከህብረተሰቡ እና  ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ትብብሩን በማጠናከር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በቅዱሰ  ጴጥሮሰ ስፔሻላይዝድ ሆሰፒታል የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሲስተር ተወዳጅ መርሻ በበኩላቸው በወሊድ ወቅት በደም መፍሰስ ህይወታቸው የሚያልፍ እናቶችን ህይወት ለመታደግ  ደም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም ማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳን ባህል ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በእለቱ የቅዱሰ  ጴጥሮሰ ስፔሻላይዝድ ሆሰፒታል ሠራተኞች የደም ልገሳ አድርገዋል።