ምክር ቤቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

62
አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2010 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ የብድር ስምምነቶችና ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ። ምክር ቤቱ 45ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ሲያካሂድ መንግስት ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ለኤሌክትሪፊኬሽን ማስፈጸሚያ ፕሮግራምና ለከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ያደረጋቸውን ሁለት የብድር ስምምነቶችና ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል። ሁለቱ ስምምነቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የገጠር ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግና በተመረጡ 117 ከተሞች የመሰረተ ልማት ዕድገትና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያግዙ መሆናቸውን ተጠቁሟል። ብድሮቹ ከአገሪቱ የብድር አስተዳደርና ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙና ጫናቸው ያልበዛባቸው መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ስምምነቶቹ እንዲጸድቁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስተላለፉን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ምክር ቤቱ መንግስት ከሩሲያ መንግስት ጋር በጉምሩክ ዘርፍ ባደረገው የትብብርና የጋራ አስተዳደራዊ ድጋፍ ስምምነት ላይም ተወያይቷል። በዚህም ስምምነቱ የሁለቱን አገሮች ግንኙነትና ትስስር እንደሚያጠናክር ስለታመነበት አዋጁ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ገልጿል። በሌላ በኩል የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ እላቂ /ቆሻሻ/ የአካባቢ ጉዳት ለማስቀረት የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ አያያዝን ለመደንገግ በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ ስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ ማሳለፉን በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም