በጋምቤላ ክልል ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች የሚፈጥሩትን የፀጥታ ስጋት ለማስወገድ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች የሚፈጥሩትን የፀጥታ ስጋት ለማስወገድ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ
ጋምቤላ ጥር 30/2011 በጋምቤላ ክልል ድንበር ዘለል የሙርሌና የፈላታ አርብቶ አደሮች በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጥሩትን የፀጥታ ስጋት ለማስወገድ ትኩረት እንዲሰጥ የክልሉ ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡
ምክር ቤቱ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ተወያይቷል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በዚሀ ወቅት እንዳሉት መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጸጥታ ስጋት የሚፈጥሩ ድንበር ዘለል ችግሮችን መከላከል አለበት፡፡
በተለይም ድንበር ተሻጋሪ አርብቶ አደሮች ጉዳይ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ በስደተኞች እየተፈጠረ ያለው ችግር መፍትሄ ያሻዋል ብለዋል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አታርፋም ሙስተፋ እንዳሉት በክልሉ ሕዝብ ላይ የፀጥታ ስጋት የሚፈጥሩ ድንበር ዘለል የሙርሌ ጎሳዎች ችግር ከማድረሳቸው በፊት ትኩረት እንዲደረግባቸው አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ያለው ስደተኞች በአካባቢው ኅብረተሰብ እየፈጠሩት ላለው ችግር መፍትሄ ይበጅለት ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኡጋላ ኡጁሉ የፈላታ አርብቶ አደሮች በክልሉ ሕዝብ ላይ እያስከተሉት ያለው ችግር አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልገዋል ይላሉ፡፡
በክልሉ የሚስተዋለውን የሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች ዝውውርና የደን ጭፍጨፋን ለማስቀረትም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባና በተለይ የገጠር መንገዶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት ከኅብረተሰቡ ይልቅ አመራሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመቀየር መሰራት እንዳለበት የሚናገሩት ሌላው የምክር ቤቱ አባል ኢንጅነር ኡሊሮ አፒየው ናቸው፡፡
ለክልሉ ወጣቶች ሥራ በመፍጠር ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መንገድ ሊመቻች እንደሚገባም አመልክተዋል።
ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ብርሃኑ ደጀኔ በክልሉ ያለው ጠቅላላ ሆስፒታል የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ሆስፒታል የሚገነባበት መንገድ እንዲፈለግ ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ በተደጋጋሚ የሚታየው የበጀት አጠቃቀም ጉድለትና ከገቢ አሰባሰብ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ማቃለል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ የጸጥታ ስጋት የሚፈጥሩ ድንበር ዘለል የሙርሌና የፈላታ አርብቶ አደሮችን በሰላማዊ መንገድ ከክልሉ የሚወጡበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
ከገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም ጋር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ዘርፉን በሰው ኃይል ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ደን ጭፍጨፋ የሚያካሂዱ አካላትም በሕግ እንደሚጠየቁም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ በትናንት ውሎው የክልሉን 2011 የበጀት ዓመትን የግማሽ ዓመት አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲሁም የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ኦዲት ሪፖርት በማዳመጥ ውይይት አድርጎበታል፡፡