ሠራዊቱ አስተማማኝ ሰላምን በማረጋገጥና የሕዝብን ደህንነት በመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው -ሜ/ጄ ጌታቸው ጉዲና

786

ሽረእንዳስላሴ ጥር 30/2011 የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት አስተማማኝ ሰላምን በማረጋገጥና የሕዝብን ደህንነት በመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ዋና አዛዡ ገለጹ።

ሰባተኛው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ትናንት በፓናል ውይይት ተከብሯል።

ዋና አዛዡ  ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ሠራዊቱ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ በመሆን የአገርን አስተማማኝ ሰላም በማስከበርና ለሕዝብ ደህንነት በመሥራት ተልዕኮውን በመወጣት ላይ ነው።

ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት ተምሳሌት መሆኑንና ኅብረ ብሔራዊነትን ተላብሶ ግዳጁን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሠራዊቱ ከሕዝብ አብራክ የተፈጠረና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር ያስመሰከረ የሰላም ኃይል በመሆኑም ተልዕኮውን በተሟላ ቁመና ያሳካል ብለዋል።

ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን ከማሳካት በተጓዳኝ የልማት አጋርነቱን በማጎልበት ሕዝቡን ከድህነት ለማውጣትና በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ተሳትፎውን እንደሚያጠናክር ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ተናግረዋል።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)ና የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ ባህሪውንና ወገንተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል።

”የሠራዊቱ ጥንካሬ ሕዝብ ነው”ያሉት አቶ ጌታቸው፣ሕዝቡ በሠራዊቱ ጥርጣሬ ሊያድርበት እንደማይገባ ገልጸዋል።

ንብረእድ ተስፋይ ተወልደ ሠራዊቱ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲንቀሳቀስ ከሕዝቡ ስጋት የወለደው መጨናነቅ እንዳስተዋሉና ስጋቱ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጎን መቆሙን አረጋግጫለሁ ብለዋል።

በትግራይና በአማራ ክልሎች ያለውን ስጋት ለመፍታት ሠራዊቱ ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረብ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በዓሉ ዛሬ ወታደራዊ ትርዒቶች  በማሳየት ይጠቃለላል ተብሎ ይጠበቃል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሠራዊት ቀን የካቲት 7 ቀን 2011 በአዳማ ከተማ ይከበራል።