የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን መመስረቻ ስምምነት በኢትዮጵያና ጊኒ መካከል ተፈረመ

91

አዲስ አበባ ጥር 30/2011 ኢትዮጵያና ጊኒ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን መመስረቻ ስምምነት መፈራረማቸው ተገለጸ ።

የሁለቱ አገሮች የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባም በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና የጊኒው አቻቸው ማማዲ ቱሬ ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን ቀደም ሲል በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረሙት የሁለትዮሽ ግንኝነት ስምምነትም ተገምግሟል።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን መቋቋም የሁለቱን አገሮች የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ ያጠናክራል።

በቀጣይም በመሪዎች ደረጃ የሚደረገውን ውይይት ተከትሎ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነትን ጨምሮ በትምህርት፣ ጤና፣ በፋይናንስና ማኔጅመንት፣ በግብርና፣ ባህልና ቱሪዝም መስኮች የትብብር ስምምነቶች ይፈረማሉ።

ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቷን ከአፍሪካ አገሮች ጋር ማጠናከር ትሻለች።

የጋራ ኮሚሽኑ በቀጣይም ዓመታዊ ስብሰባቸውን በማድረግ በሁለቱ አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ እንደሚመክሩም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ገልፀዋል።

የኢትዮ - ጊኒን የትብብር ስምምነት ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋርም ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቷን ማጠናከር እንደምትሻ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

የጊኒ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ማማዲ ቱሬ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራትም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልፀዋል።

የሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት የከፍተኛ ኤክስፐርቶች ቃለ ጉባኤ ስምምነትም በዛሬው እለት ተፈርሟል።

ኢትዮጵያና ጊኒ በቀድሞ መሪዎቻቸው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና በፕሬዝዳንት ሴኩ ቱሬ አማካኝነት የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በግንባር ቀደምትነት የመሰረቱ አገሮች ናቸው።

ሁለቱ አገሮች የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን የጀመሩት በ1950 ዓ.ም ሲሆን ጊኒ ሪፐብሊክ  በ1962 ዓ.ም ኤምበሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም