የጊኒ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

117

አዲስ አበባ ጥር 29/5/2011 የጊኒ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ።

ፕሬዚዳንቱ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተቀብለዋቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው የመጀመሪያው የኢትዮ-ጊኒ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ምስረታ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ እንደሚሳተፉ ታውቋል።

በኢትዮጵያና በጊኒ መካከል ስትራቴጂያዊ አጋርነት የሚመሰርት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የሚቋቋም ሲሆን፣ ዛሬ የኮሚሽኑን ምስረታ አስመልክቶ የባለሙያዎች ስብሰባ ተጀምሯል።

ባለሙያዎቹ ተወያይተው ያዘጋጁትን ረቂቅ ሰነድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የጊኒ አቻቸው ማማዲ ቱሬ  እንደሚፈራረሙም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ በትምህርት፣ በግብርና፣ በባህልና ቱሪዝም መስኮች ለመተባበር የሚያስችል ስምምነቶች ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያና ጊኒ በቀድሞዎቹ መሪዎቻቸው በንጉስ ኃይለስላሴ እና በፕሬዚዳንት ሴኮ ቱሬ አማካይነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የአሁኑ የአፍሪካ ህብረትን የመሰረቱ ግንባር ቀደም አገሮች ናቸው።

አገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት በ1950 ዓ.ም ሲሆን ጊኒ ሪፐብሊክ ኤምባሲዋን በ1962 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ከፍታለች።

የሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጊኒ ሪፐብሊክ ጋር የሚካሄደውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደሚያከናውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም