በኅብረቱ ጉባዔ ላይ የአገር መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ይታደማሉ

70

አዲስ አበባ ጥር 29/2011 በሳምንቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ 40 የአህጉሪቱ መሪዎችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ይካፈላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጉባዔው የኢትዮጵያንና የአፍሪካዊያንን ባህል በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲከናወን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

32ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአባል አገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አማካኝነት ነገ የሚጀምር ሲሆን የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ የመሪዎቹ ስብሰባ ይካሄዳል።

የዘንድሮ ጉባዔ ዋና አጀንዳ የኅብረቱን የለውጥ ተቋማዊ አደረጃጀትና እንቅስቃሴ ያለበት ሁኔታ መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው።

"አስተማማኝ መፍትሄ በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚፈናቀሉ አፍሪካዊያን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች" የሚለው አጀንዳ የኅብረቱ አባል አገሮች ዓመቱን ሙሉ የሚሰሩበት እንደሆነም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ነገ በሚጀመረው የኅብረቱ አባል አገሮች የሚኒስትሮች ስብሰባና የመሪዎች ጉባዔ ለመታደም ከአህጉሪቱ መሪዎች በተጨማሪ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በሚወሰንበት አህጉራዊ ጉባዔ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አገራት መሪዎች እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የፍልስጤም መሪን ጨምሮ የኢስቶኒያ ፕሬዝዳንት፣ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትርና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ባለሃብቶች እንደሚታደሙም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔን በምታስተናግድበት ወቅት ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ እንደሚቋቋም የገለጹት አቶ ነቢያት፤ የዘንድሮ ጉባዔ በሰላምና አፍሪካዊ እሴትን ባንጸባረቀ መልኩ እንዲከናወን ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል። 

በአዲሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሉ ስካይ ሆቴል የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ባህላዊ እሴት የሚያንጸባርቅ ልዩ አፍሪካዊ መርሃ-ግብር ለመሪዎቹ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በፀጥታ፣ በትራፊክ ፍሰትና በአጠቃላይ በከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የተቋማት ጥምረት መሆኑንም ነው አቶ ነቢያት ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም