ጅግጅጋ ስምንተኛውን የከተሞች ቀን ለማስተናገድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው

62

ጅግጅጋ ጥር 29/2011 ጅግጅጋ ለምታስተናግደው የኢትዮጵያ ከተሞች  ስምንተኛ ፎረም ዝግጅቷ እያጠናቀቀች መሆኗን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

የዘንድሮው የከተሞች ቀን ''መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና!'' በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

 በፎረሙ 165 ከተሞች ይሳተፉበታል ተብሎም ይጠበቃል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አደን ፋራህ ዛሬ ከፎረሙ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት ከተማዋ ለፎረሙ የሚመጡ ከ20 ሺህ በላይ እንግዶቿን ለመቀበል እየተዘጋጀች ነው።

ፎረሙን ለማስተናገድ በከተማዋ አስተዳደርና በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የተጀመሩ ሥራዎች እየተጠናቀቁ ናቸው ብለዋል።

ፎረሙ ከተሞችን እርስበርስ ለማስተዋወቅና ለመማማር፣ ለገጽታ ግንባታ፣ ኢንቨስትመንትና ንግድን ለማጠናከር እንደሚያግዝም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልፈታ ሼህ ቢሒ ከተማዋ ለፎረሙ የሚመጡ እንግዶቿን ለማስተናገድ የማረፊያና የትራንስፖርት አገልግሎት ማዘጋጀቷን አስታውቀዋል።

ከተማዋ ከየካቲት 9-14/2011 በምታስተናግደው ፎረም እስካሁን 165 ከተሞች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ከጎረቤት አገሮች ሐርጌሳ፣ ጂቡቲ፣ ሞቃዲሾና ጋሪሳ ከተሞች ተሳታፊዎች ይልካሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ከተመሰረተች 100 ዓመታት ያህል ያስቆጠረችው የጅግጅጋ ከተማ፣ከ150 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳሏት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማዋ በምሥራቃው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ናት።

ጅግጅጋ የከተሞች ቀንን በታዳጊ ክልሎች ለማስተናገድ የመጀመሪያዋ ትሆናለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም