ፕሬዘዳንት ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ገለጹ

81

ጥር 29/2011 የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ጋር የኒኩለር መርሃ ግብርን አስመልክቶ ለሁለተኛ ጊዜ ለመወያየት በዚህ ወር እቅድ መያዛቸውን አስታወቁ፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው ፕሬዘዳንቱ ይህን ያሉት ትላንት ምሽት በዋሽግተን ዲሲ ባደረጉት ንግግር ሲሆን ውይይቱም እኤአ ከየካቲት 27-28 / 2019 በቬትናም ይካሄዳል ብለዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በንግግራቸው "ብዙ ያልሰራኋቸው ቀሪ ሰራዎች ቢኖሩኝም ከሰሜን ኮሪያው ፕሬዘዳንት ኪም ጆንግ ኡን ጋር እያካሄድኩት ያለው የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያን የማስወገድ ድርድር ግን እጅግ በሚያበረታታ ደረጃ ላይ ይገኛል"ብለዋል፡፡

የሁለቱ አገራት መሪዎች በያዝነው ወር የመጨረሻ ሳምንት በሚያካሂዱት የሁለትዮሽ ውይይትም ለሁለቱ አገራት በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው እንደሚወያዩና ከስምምነት ላይ እንደርሳለን የሚል እምነት እንዳላቸው ፕሬዚዳንቱ አክለው ተናግረዋል፡፡

የአሁኑ የውይይት እቅድ በአለፈው አመት ሲንጋፑር ላይ ሁለቱ መሪዎች ካደረጉት ውይይት የቀጠለ ነው፡፡

በ 2018 ሰኔ ወር ላይ በሲንጋፑር የተካሄደው የሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት በአገራቱ ታሪክ የመጀመሪያና ስምምነቱም በኒኩለር የጦር መሳሪያ ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በስምምነታቸው መሰረትም ከሁለቱ መሪዎች ውይይት ማግስት ጀምሮ ፒዮንጋንግ በአሁኑ ሳዓት የኒኩለር ማስወንጨፍና የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ የማምረት መርሃ ግብሯን በማቋረጥ ቃሏን ጠብቃ ትገኛለች፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው ኪም ጋር የባለፈው ውይይታቸው ፍሬያማ እንደነበር ገልፀው ቀጣዩ ውይይትም ለሁለቱ አገራት መፃዒ እድል መሰረት የምንጥልበትና ለአለም ህዝብ ምሳሌ የሚሆን ውሳኔ የምናስተላልፍበት እንደሚሆን እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም