የሃብት ብክነቱ አደጋ እና የመንግስት ቁርጠኝነት

1118

ሀብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ)

ከእያንዳንዱ የመንግስት ከፍተኛ ፕሮጀክቶች ጀርባ ፈርጀ ብዙ የሃብት ብክነት ሂደቶችን መመልከቱ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል። እንደ ሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከፍተኛ ሃብት በማፍ ሰስ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየገነባና እያስገነባ የሚገኘው መንግስት ነው። ከመንገድ እስከ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ ከኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች እስከ ባቡር መሰረተ ልማቶች፣ ከመጠጥ ውሃ ኮንስትራክሽን ግንባታዎች እስከ ግድቦች በሚሊዮኖች አልፎ ተርፎም በቢሊዮኖች የሚቀጠር ገንዘብ ባክኖ ሲቀር ይታያል።

ሲጀመሩ በሚሊዮኖች በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተቱ ደግሞ ለማጠናቀቂያ መንግስትን በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ መጠን የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች፣ በተጋነኑ ክፍያዎች የታጀቡ የሙስና ወንጀሎች፣ በግብር አከፋፈል ረገድ የሚስተዋሉ አሻጥሮች፣ ተገቢ የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድባቸው እዚህም አዚያም የተጀማመሩ ፕሮጀክቶች ለህዝብና መንግስት ሃብት ብክነት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣቸው የተቋማት የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች የሚያመላክቱት ጉዳይ ቢኖር የተቋማቱ የበጀት አጠቃቀም ዝርክርክነት መንግስትን ለከፍተኛ የሃብት ብክነት እየዳረገው እንደቆየ ነው። በኦዲት ግኝት ሪፖርቶቹም ላይ የመንግስትን የፋይናንስ ህግ ሳይከተሉ የተከናወኑ ግዥዎች እንዲሁም ተቋማቱ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት  ያደረጉትን ወጪ ያለማወራረድ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው አሳይተዋል።

የመንግስት ወጪ ሂሳብ በ7 ቀናት ውስጥ መወራረድ ዳገት ነው

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ መሠረት ማንኛውም የመንግስት ወጪ ሂሳብ በ7 ቀናት ውስጥ መወራረድ ቢገባውም ተቋማቱ ግን ጉዳዩ ዳገት ሆኖባቸው ወደ ተግባር ሲለውጡት አልታዩም። ከቅርብ አመታት በፊትም በ113 የመንግስት ተቋማትና በ28 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ላይ ተከናውኖ በነበረው የኦዲት ምርመራ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሂሳብ ተገኝቷል። ከዚህ ውስጥ ከ375 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተመዘገበና ከማን እንደሚሰበሰብ አለመታወቁ ደግሞ ምን ያህል የህዝብ ሃብት እየባከነ ለመሆኑ ማሳያ ነው።

የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከላይ ከተጠቀሰው ጉዳይ ጋር በተያያዘ በችግሩ በሰፊው ተዘፍቀውበት ከሚገኙት ይጠቀሳሉ። የተቋማቱ አመራሮች ለዘመናት ያልተወራረዱ የሂሳብ መዝገቦችን ለማወራረድ እያሳዩት የሚገኘው የቁርጠኝነት መታጣት ችግሩን ለመቅረፍ እየተደረገ በሚገኘው እርምጃ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎበት ሰንብቷል። በዚህም ሳቢያ የመንግስትን ገቢ በወጡ ህጎች መሰረት መሰብሰቡን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት ደግሞ ሌላ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡ መረጋገጡም በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ከውዝፍ ግብር፣ ከወለድ እንዲሁም ከተለያዩ ቅጣቶች መሰብሰብ የነበረት 4 ቢሊዮን ብር አካባቢም እንዲሁ ሳይሰበሰብ ባክኖ መቅረቱንም ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት መግለፁ ይታወሳል።

ከኦዲት ግኝት ሪፖርት ጋር በተያያዘም የኢትዮዽያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሊገነባቸው አቅዷቸው ከነበሩ የስኳር ፕሮጀክቶች ሶስቱ ውላቸው እንዲቋረጥ የተደረገበትንም የቅርብ ጊዜ ክስተት ማየት ይቻላል። እንደ መረጃው ሜቴክ ፕሮጀክቶቹን ለመፈፀም ተጨማሪ የስድስት ወራት የማራዘሚያ ጊዜ ቢሰጠውም ግንባታውን ሊፈፅም አልቻለም። በዚህም ሳቢያ የበለስ አንድና ሁለት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የኦሞ ኩራዝ አንድ የስኳር ፋብሪካ ውሎች እንዲቋረጡበት ተደርጓል። በጥቅሉም ኮርፖሬሽኑ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ማባከኑም በኦዲት ምርመራ መረጋገጡን ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ ሪፖርት ላይ መገለፁም የሚታወስ ነው። በዚህም ረገድ የፌደራል ዋናው ኦዲተር ሚና የገዘፈ እንደነበርም ከወራት በፊት ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።

መንግስት በሚሌኒየሙ ማግስት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ማስጀመሪያ ወቅት በርካታ ሰፋፊና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ የጀመራቸው የተለያዩ ግንባታዎች ከአስርተ አመታት በኋላ ኢምንት የሆኑት ስኬታማ ሲሆኑ በርካቶቹ ከመሰረት ድንጋይ ማኖር አልዘለሉም። ጥቂቶቹን ወደ ተግባር ለመለወጥ መንግስት ጥረቶችን እያደረገ ቢገኝም በቆይታ ደለብ ያለ የመንግስት በጀቶችን እየጠየቁ ከፍተኛ ኪሳራን ከማስከተላቸውም በላይ አገሪቷ ከባድ የዕዳ ጫና እንዲተርፋት እያደረጉ ይገኛሉ።

የመገጭን የመስኖ ግድብ ለአብነት የወሰድን እንደሆነ ግድቡ ከጅምሩ የአዋጭነት ጥናት ያልተሰራለት ከመሆኑም ባሻገር ዲዛይኑ በየጊዜው እንዲቀያየር በመደረጉም ጭምር በ2 ቢሊዮን 451 ሚሊዮን 923 ሺህ 789 ብር ለመገንባት ውል ቢታሰርም አሁን ላይ ግድቡን ለመገንባት ከ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መጠየቁን ማንሳት ይቻላል።

ይህም ግድቡ ቀድሞ ከተያዘለት በጀት የ53 በመቶ ጭማሪ ወጪን እንደጠየቀ ያሳያል። እንግዲህ በወቅቱ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለከፍተኛ  የመንግስትና ህዝብ የሃብት ብክነቶች አይነተኛ ማሳያ እንደሆኑ መገጭን የመሰሉ የመስኖ ግድቦች ምስክር ናቸው።

ሌላው ለሃብት ብክነቱ አሳሳቢነት ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ደግሞ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከ2003 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ባለው ጊዜ መጠናቀቅ ከነበረባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነበር።

ይሁን እንጂ ግንባታው ተጓቶ አፈፃፀሙ ከ44 በመቶ ማለፍ አልቻለም። ከዚያም የማጠናቀቂያ ዕቅዱን ወደ 2008 ዓ.ም ከዚያም ወደ 2009 ቀጥሎም በ2010 ዓ.ም አድርጎም ሊጠናቀቅ ቀርቶ በወጪ ላይ ወጪን እየደረበ አሁን ያለንበት አመት ላይ ደርሷል።

የፕሮጀክቱ ሂደት እጅግ አዝጋሚ ከመሆኑም ባሻገር በየወሩ 90 ሚሊዮን ብር የባንክ ወለድ እየተከፈለ እስካሁን ለተጠቀሰው ጉዳይ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተከፍሏል። ይህም ሆኖ የፕሮጀክቱ ግንባታ 50 በመቶ እንኳን አልተጠናቀቀም። የሃብት ብክነትን በተለየ ሁኔታ ለመግለፅ ከዚህ የበለጠ ማሳያ ማቅረብ ይቻል ይሆን?

በሌላም በኩል አመታዊ ገቢያቸው ሚሊዮኖችን የተሻገሩ ባለሃብቶ ያለደረሰኝ መገበያየት፣ የመጠናቀቂያ ጊዜያቸው የተሻገሩ የመንገድ፣ የቤት እና መሰል መሰረተ ልማቶች፣ ለአመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ያባከኑትን የህዝብና የመንግስት ሃብት ቤቱ ይቁጠረው። ለዘመናት ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ለህዝብ ጠቀሜታ የሚውሉ ተግባራት ቢከወንባቸው ኖሮ ያመጡት የነበረውን ማህበራዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ጠቀሜታ ሲታሰብ የሃብት ብክነት ምን ማለት እንደሆነ በቀላሉ ለመረዳት ያስችላል።

በመንገድ መሰረተ ልማትም ቢሆን በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ለመገንባት ከታሰበው 90 ሺ ኪሎ ሜትር መንገድ ለመፈፀም የተቻለው 9ሺ 557 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ይህም አፈፃፀሙ የዕቅዱን 21 በመቶ ማለት ሲሆን በዚህም ውስጥ የባከነውን ሃብትና ንብረት መገመት አያዳግትም።

በያዝነው አመት መጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በታቀደና በተቀናጀ መልኩ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ መናገራቸው መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ቁርጠኛ መሆኑን ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሞ ኩራዝ 3 የስኳር ፕሮጀክት በመረቁበት ወቅትም መንግስት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ብቻም ሳይሆን ጅምር ፕሮጀክቶችን የመጨረስ አቅም እንዳለው ማሳያ እንደሆነም ተናግረው ነበር።

ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው ከፍተኛ የሙስና ወንጀሎችን በመፈፀም የህዝብና የመንግስት ሃብት እንዲመዘበር ያደረጉ ግለሰቦች በህግ የመጠየቅ ቁርጠኛ አቋም የያዘው የመንግስት ተቋማት የፋይናንስ አሰራሮቻቸውን በመከለስ ከብክነት የፀዳ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉም የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል።

ለዚህም እንደማሳያ ቀደምሲል በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የነበሩ የመንግስት ባለስልጣናትን ተጠያቂ የማድረጉ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን መጥቀስ ይቻላል። መንግስት የተደራጀ ስራ በመስራት ሙሰኞችን ለማጋለጥ እንደሚተጋም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በ4ተኛው አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጉባኤ ላይ ተገኝተው መናገራቸውም የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም።

የቅርቡን ብናስታውስ እንኳን ከጥረት ኮርፖሬት ጋር በተያያዘ በፈፀሙት የሃብት ብክነት ተጠርጥረው  በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ  በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ከሰሞኑ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለመረዳት ተችሏል። ግለሰቦቹ ከፋይናንስ አሰራርና ህግ ውጪ 7 ሚሊዮን ብር ለሁለት ኩባንያዎች እንዲሰጥ አድርገዋል፤ አንድ ሺ ብር የሆነን የአክሲዮን ዋጋ በ2ሺ 220 ብር እንዲገዛ በማድረግ የ4 ሚሊዮን 320 ሺህ ብር በህዝብ ሃብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚልና በሌሎች ጉዳዮች ተጠርጥረው ለህግ እንደቀረቡም ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል።

ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ አመታት በርካታ የኦዲት ጉድለት ሪፖርቶችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ የነበረው የፌደራል ዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት በተቋማቱ በኩል እምብዛም ለውጥ እየታየ እንዳልሆነ በዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በኩል የገለፀ ሲሆን፤ ሆኖም መንግስት አሁን እያሳየ የሚገኘው ቁርጠኛ አቋም በ2011 በጀት አመት መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል በመስሪያ ቤቱ ተስፋ ተጥሎበታል።