በመቻራ ከተማ የኤሌትሪክ ኃይል ለዘጠኝ ወራት በመቋረጡ ተቸግረናል - ነዋሪዎች

60
ጭሮ ግንቦት 20/2010 በምእራብ ሀረርጌ ዞን የመቻራ ከተማ ነዋሪዎች የኤሌትሪክ አገልግሎት ላለፉት ዘጠኝ ወራት በመቋረጡ ለችግር መጋለጣቸውን ገለፁ ። በዞኑ ዳሮለቡ ወረዳ የመቻራ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለፁት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለረጅም ጊዜ በመቋረጡ ምክንያት የጋራጅ ፣ የወፍጮ ፣ የፎቶግራፍና የፀጉር ማስተካከያና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት አልቻሉም። በመሆኑም እነዚህን  አገልግሎቶች ፍለጋ ወደ ተለያዩ  አካባቢዎች በመዘዋወር ለእንግልትና ላልተፈለገ  ወጪ ተዳርገናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሁሴን አሊዪ በሰጡት አስተያየት ''ላለፉት ዘጠኝ ወራት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አላገኘንም ፤ ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች ብናሳውቅም እስካሁን መፍትሔ አልተሰጠንም'' ብለዋል ። ወይዘሮ መሰሉ ከበደ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው ለቀለብ ፍጆታ የሚሆን እህል ለማስፈጨት ኤሌትሪክ  ወዳለበት ሌሎች  አካባቢዎችን በማሰስ  ረጅም ርቀት  ለመጓዝ እንደተገደዱና በዚህም አላስፈላጊ ለሆነ የጊዜና የገንዘብ ብክነት እየዳረገቸው መሆኑን በምሬት ገልፀዋል ። ''ለችግሩ መፍትሔ ለማፈላለግ  ከክልል እስከ ፌዴራል መንግስት ድረስ  አቤት ብንልም እስካሁን መፍትሔ ማግኘት አልቻልንም ''ያሉት ደግሞ የከተማዋ የሀገር ሽማግሌ አቶ መሀመድ ቡሎ ናቸው፡፡ የከተማዋ የመብራት አገልግሎት መቋረጠ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠን ጠይቀዋል፡፡ ''የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ሆኑ የግል ድርጅቶች የኤሌትሪክ ኃይል ማግኘት ባለመቻላቸው ጄኔሬተር በመጠቀም ለተጨማሪ ወጪ ተጋልጠዋል'' ያሉት ደግሞ የዳሮለቡ ወረዳ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ ደስታ ዱቤ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የምስራቅ ሪጅን ኮንሲመር ግሪቫንስ ሀላፊ አቶ ታምሩ አምሳሉ ስለሁኔታው ተጠይቀው ነዋሪዎቹ ያነሱት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ችግሩ የተፈጠረው ለከተማዋ መብራት የሚሰጠው መስመር ያረጀና  ከሰብስቴሽኑ ሩቅ በመሆኑ ችግሩ የተከተሰበትን አካባቢ ለይቶ ለመፍታትት ረዢም ጊዜ በመውሰዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መስመሩ ላጋጠመው ችግር ዘላቂ  መፍትሔ ለመስጠት ያረጁትን መስመሮች ሙሉ በሙሉ በአዲስ ለመተካት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም